
ጎንደር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትትዮጵያ ሀገር አቀፍ የመንገድ ዘርፍ ጉባኤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር) የመንገድ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ሀገሪቱን ለማሳደግ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት በማሳደግ በኩልም በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ የፌዴራል መንግሥት 66 የሚደርሱ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ፈቃድ መስጠቱን ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከአሁን በፊት ይነሳ የነበረውን የፍትሐዊነት ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንገድ መሠረተ ልማቱን በማሳለጥ በኩል የፌደራል መንግሥቱ ትኩረት በመስጠት እየሥራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማፋጠን ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል። የሀገሪቱን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ከለውጡ በፊት ከነበረው 126 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ሽፋን ወደ 171 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር ማድረስ ተችሏልም ብለዋል።
አሁን ላይ በፌደራል ደረጃ 51 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 160 የሚደርሱት ደግሞ በግንባታ ላይ መኾናቸውም ተገልጿል። የመንገድ ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የጸጥታ ችግሩ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሰደሩም ተመላክቷል። በጸጥታ ችግር እያለ በተሻለ ለመፈጸም እየተሠራ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል የግንባታ ግብዓት አቅርቦት አንዱ ፈተና መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሯ ችግሩን ለመቅረፍ የፌደራል መንግሥቱ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በቀጣይም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሳልጡ የሚችሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይገነባሉም ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን ባለፉት ስድስት ወራት የተቋረጡ አራት ፕሮጀክቶች እንደ አዲስ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። አምስት ፕሮጀክቶች ደግሞ በአዲስ ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል የግንባታ ቦታዎች ከሦስተኛ ወገን አለመጽዳት እና የካሳ ክፍያ እንቅፋት መኾናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የካሣ ክፍያን በመክፈል በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:-ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!