የሕዝብ ሰላምን ለማወክ ሊውል የነበረ ተተኳሽ ተያዘ።

71

ሁመራ: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በተከዜ ወንዝ ዳርቻ አካባቢ የተያዘው የዲሽቃ ተተኳሹ 30 ሳጥን ነው። ከ2 ሺህ 700 ፍሬ በላይ መኾኑን በጥምር ኅይሉ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኅላፊ ኮማንደር ሙላት ማሞ ገልጸዋል።

ኮማንደሩ የዚህ ተተኳሽ መያዝም ጥምር ኀይሉ ሰላምን ለማጽናት ከሚሠራቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱ ነው ብለዋል። ተተኳሽ ጥይቱ ወደ መሐል ሀገር ሊዘዋወር እንደነበር ያስረዱት ኮማንደር ሙላት የሕዝብን ሰላም ለማወክ ሊውል እንደነበርም አስረድተዋል። ሕዝብን ለማወክ፣ ተቋማትን እና መሠረተ ልማትን ለማውደም ብሎም ሀገሪቱን ለመበጥበጥ ታስቦ እየተንቀሳቀሰ ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ የተደራጀ እና የተቀናጀ የጸጥታ መዋቅር በመኖሩ ተተኳሹን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ነው ኮማንደሩ ያስታወቁት። ጥምር ኀይሉ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር የውስጥን ሰላም ለማጽናት በትጋት እየሠራ መኾኑን ኮማንደር ሙላት አስረድተዋል።

በቀጣናው የመከላከያ ሠራዊት ሰላምን የማጽናት ድርሻ የጎላ ነው ያሉት ኮማንደር ሙላት ከፖሊስ፣ ከሚሊሻ እና ከሰላም አስከባሪ ኀይሉ ጋር ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ተልዕኮውን እና ግቡን ለማሳካት ጥምር ኀይሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ተናቦ እየሠራ እንደኾነ ያስረዱት ኮማንደር ሙላት የዚህ ተተኳሽ መያዝም አንዱ ማሳያ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሚና ጥምር ኀይሉን ከመምራት ባለፈ ለሚሊሻው እና ለሰላም አስከባሪ ኀይሉ በአቅም ግንባታ፣ በወታደራዊ እና ሙያዊ ድጋፍ፣ በቁሳቁስ የሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ መኾኑን ኮማንደር ሙላት ተናግረዋል። ሰላምን ለማጽናት የጥምር ኅይሉ የተቀናጀ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደረሰኝ ህትመት ጥያቄ የማቅረቢያ ቀነ ገደብ መሻሻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየመጀመሪያው ምዕራፍ የሀረር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ