
ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ልዩ የመለያ ኮድ (QR Cod) የተካተተበት የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ የማቅረቢያ ቀነ ገደብ እስከ የካቲት 30/ 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም የተወሰነ መኾኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ ቀደም የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ ማቅረብ የሚቻለው እስከ ጥር 30 ድረስ ብቻ እንደኾነ በተገለጸው መሠረት ቁጥራቸው 88 ሺህ 717 የኾኑ ግብር ከፋዮች የህትመት ጥያቄ ማቅረብ መቻላቸውን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ተናግረዋል።
ከክልል እና ከተማ አሥተዳደር የገቢ ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ባደረጉት ውይይት ነው ይህን ያሉት፡፡ ኾኖም በተለያዩ ምክንያቶች የህትመት ጥያቄያቸውን ያላቀረቡ ግብር ከፋዮች መኖራቸው ታሳቢ በማድረግ የህትመት ጥያቄ ማቅረቢያ ቀነ ገደብ እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም በውይይቱ እንደተወሰነ ከገቢዎች ሚኒስቴር የትስስር ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
እንደ ሀገር በገቢው ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ በውይይቱ ገልጸዋል። በተለይም የማንዋል ደረሰኝ አጠቃቀም እና አሥተዳደር ሥርዓትን በማሻሻል የሚፈለገውን የገቢ ዕድገት ማረጋገጥ ያሰፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) የተካተተበት ሚስጥራዊ የደረሰኝ ህትመት ሥርዓትን ወደ ተግባር ማስገባት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መኾኑን ያስገነዘቡት ሚኒስትሯ እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊ የኾኑት የክልል እና ከተማ አሥተዳደር የገቢ ዘርፍ መሪዎች ሕገ ወጥነትን እና የታክስ ማጨበርበር ወንጀሎችን ከመከላከል አንጻር የደረሰኝ አጠቃቀም እና አሥተዳደር ሥርዓታን በልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) የተደገፈ እንዲኾን መደረጉ ተገቢ እና ተክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
እስከ አሁን በነበርው የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ እና ስርጭት ሂደት በተስተዋሉ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በተለይም አንዳንድ ግብር ከፋዮች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በተሟላ መለኩ የህትመት ጥያቄያቸውን ያለማቅረብ፣ የሲስተም መቆራረጥ፣ ህትመት እና ስርጭት መዘግየት እንዲኹም የመረጃ ልውውጥ ክፍተቶች መታየታቸውን ተጠቅሷል፡፡
የታዩ ክፍተቶችን ማረም እንዲቻል በተለይም እስከ አሁን ድርስ የህትምት ጥያቄ ያላቀረቡ ግብር ከፋዮች በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የህትመት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጠ ነው ተብሏል። የሲስተም መጨናነቅ እንዳይፈጠር ማሻሻያዎችን ማከናወን፣ የህትመት እና ስርጭት ተግባራት በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን ተጨማሪ የህትመት ማሽኖችን ወደ ሥራ ማስገባት እና አትሞ በፍጥነት ማሰራጨት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ሌሎች መሰል ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሁሉም ድርሻ ወሳኝ በመኾኑ የክልል፣ የከተማ አሥተዳደር እና የፌዴራል የገቢ ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች፣ ፈጻሚዎች፣ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅ እንድኹም ግብር ከፋዮች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!