የመንግሥት ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ ትኩረት ይደረጋል።

48

ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን እና የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ረፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኀይል ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺአምላክ ገብረማርያም የተቋማትን የመፈፀም አቅም ለማሻሻል እና በአሠራር ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በ1 ሺህ 226 የመንግሥት ተቋማት ድጋፍ እና ክትትል መደረጉን ገልጸዋል።

ተቋማት አሠራርን ለማዘመን በዲጂታላይዝ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን፣ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ፣ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ፣ ጤና ቢሮ እና ወሳኝ ኩነቶች ለአብነት ተነስተዋል።

በስድስት ወሩ ከተለዩት 11 ሺህ 485 የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ውስጥ 5 ሺህ 649 ያህሉ ምላሽ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይም የመንግሥት ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያመላኩት።

የዲጂታላይዜሽን፣ የሠራተኞች የሙያ ብቃት ምዘና፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት አና ሌሎችንም ሥራዎች በተደራጀ መንገድ ለማክናዎን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የቢሮው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም ባለፉት ስድስት ወራት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በትምህርት ምዝገባ፣ በሰብል አሠባሠብ፣ በሰላም እና ጸጥታ፣ በኮሌራ ወረርሽኝ መከላከል እና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት፣ የመስኖ ልማት፣ ሀገራዊ መግባባት ሌላው ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ እንደነበር ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡ በሃሰተኛ መረጃ እንዳይደናገር ትኩረት ተሠጥቶ መሠራቱንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሽምግልና መማክርት ጉባኤ ለማቋቋም ማስፈጸሚያ ሰነድ እና የመመስረቻ ጽሑፍ መዘጋጀቱን የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየደረሰኝ ህትመት ጥያቄ የማቅረቢያ ቀነ ገደብ መሻሻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።