
ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ ባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ ሥራዎችን ለቋሚ ኮሚቴ አባላት አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን የመለየት፣ የማልማት እና የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
በስድስት ወሩ ከ11 ሺህ 158 የውጭ ጎብኝዎች 34 ሚሊዮን 735 ሺህ 331 ብር መገኘቱን ኀላፊው ገልጸዋል። ከ5 ሚሊዮን 401 ሺህ 631 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ደግሞ 2 ቢሊዮን 481 ሚሊዮን 481 ሺህ 29 ብር ተገኝቷል ብለዋል።
ከሀገር ውስጥም ኾነ ከውጭ ጎብኝዎች የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ በላይ መኾኑ ነው ያነሱት።
ባለፉት ስድስት ወራት ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች የመለየት እና የጥገና ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።
የሽምግልና መማክርት ጉባኤ ለማቋቋም ማስፈጸሚያ ሰነድ እና የመመስረቻ ጽሑፍ ተዘጋጅቷል። በ17 ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና ባሕላዊ እሴቶች ላይ ጥናት ተደርጓል። በዕደ ጥበባት ለተሰማሩ ባለሙያዎች የፈጠራ ክሕሎት ሥልጠና ተሠጥቷል።
ለ1 ሺህ 329 ዜጎች ቋሚ፣ ለ11 ሺህ 142 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 83ቱ አካል ጉዳተኞች ናቸው።
በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ ለባሕል ተቋማት እና ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችን ከመረጃ ማሠባሠብ ያለፈ ሥራ አለመሠራቱ፣ ቢሮው የኢንቨስትመንት ቦርድ አባል አለመኾኑ ለአሠራር እና ለመረጃ ችግር መፍጠሩ እንደ ችግር ተነስቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!