
ጎንደር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ባለፉት ስድስት ወራት በፋሽን ዲዛይን፣ በአይ ሲቲ፣ በሽመና፣ በእንጨት እና ብረታ ብረት ሥራዎች ያሠለጠናቸውን የ2017 ዓ.ም አንደኛ ዙር ሠልጣኞችን አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ አካል ጉዳተኝነት የትኛውም ሰው ላይ ሊያገጥም የሚችል መኾኑን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች በአካል ጉዳት ምክንያት የሚደርስን ጫና በመከላከል እና በራስ መተማመንን በመገንባት ለሌሎች አርዓያ እንደሚኾኑ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። የይቻላል መንፈስን መፍጠር እንደሚችሉም አመላክተዋል።
የሙያ ሥልጠናን ያገኙ አካል ጉዳተኞች የሥራ እድሎችን እንዲያገኙ እና በቀጣይ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
የጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ኀላፊ ቤተልሔም አዱኛ ማዕከሉ ከ1963 ጀምሮ የተቋቋመ መኾኑን አስታውሰዋል። ማዕከሉ አካል ጉዳተኞች የራሳቸውን አሻራ እንዲያበረክቱ በማለም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ በየዓመቱ እስከ 500 የሚደርሱ ሠልጣኞችን እንደሚያሠለጥንም ተናግረዋል። ዛሬ ያስመረቃቸው ሠልጣኞች 149 ናቸው።
ተመራቂ ሠልጣኞችም ከማዕከሉ ባገኙት የሙያ ሥልጠና መሠረት በሠለጠኑበት ሙያ ላይ ተሰማርተው ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች ሥልጠናዎችን ወስደው እንዲሠሩ እና በሥነ ልቦና ጠንካራ እንዲኾኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። ማዕከሉ ከሙያ ሥልጠና ባሻገር የሥነ ልቦና ድጋፍ፣ የሕክምና እና ሌሎችም አስፈላጊ እገዛዎችን ለሠልጣኞች እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን