የጸጥታ ችግሩ በግብር አሰባሰቡ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

33

ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ክትትል የሚያደርግባቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ የበሮውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም በ2017 ዓ.ም 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። እስካሁን 27 ነጥብ 119 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል። አፈጻጸሙም 37 ነጥብ 85 በመቶ መኾኑንም አመላክተዋል።

ከከተማ አሥተዳደሮች ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና ወልድያ ከዞኖች ደግሞ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ዋግ ኽምራ የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ገልጸዋል። በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ለገቢ አሰባሰቡ እንቅፋት መኾኑን ያመላከቱት ኀላፊው በስድስት ወራት መሰብሰብ ካለበት ገቢ የተሰበሰበው ገቢ 76 ነጥብ 47 በመቶ መኾኑን ገልጸዋል። 394 ሺህ 286 ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ያለ ቅጣት እንዲከፍሉ ታቅዶ መሠራቱን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብር አሰባሰብ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ እና ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ መሠራቱንም ተናግረዋል። የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የንቃተ ግብር እና ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

የመረጃ ልውውጥን በየቀኑ በማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።

በስድስት ወራት በወቅታዊ ክልላዊ ችግር ምክንያት የታክስ ሕጎች አለመጽደቅ፣ በግጭቱ ምክንያት የተቋማት መዘረፍ እና ሌሎች ችግሮች እንደገጠሟቸው ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጸጥታ ችግር የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አሳወቀ።
Next articleአካል ጉዳተኞች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ይሠራል።