
አዲስ አበባ: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስትር የ2017/18 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) መንግሥት የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መኾኑን አንስተዋል።
በዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን ከባለፈው ዓመት 4 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ በማድረግ 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈፀም ታቅዷል ብለዋል። ለዚህ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚውል 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ በመደረጉ በእስካሁን የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ትልቅ ድጎማ የተደረገበት ዓመት እንደኾነ አንስተዋል።
እስካሁን 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈፀሙን እና ከዚህ ውስጥ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው ጂቡቲ ወደብ መድረሱን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው ተናግረዋል። በባለፈው ዓመት ከተረፈው ወደ 3 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ጋር አጠቃላይ 7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መኖሩን አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!