
ባሕር ዳር: ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ እና የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ላይ በባሕር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ውይይቱ የጉባኤውን ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ወደ ሁሉም መሪዎች እና ወደ ሕዝቡ በማውረድ እና ለሀገር እድገት በሚበጅ መልኩ በተግባር ለመተርጎም ያለመ ነው ብለዋል።
የክልሉ ወቅታዊ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተነስተው ምክክር እንደሚካሄድ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም አመላክተዋል።
የተቋማትን የሥራ አፈጻጸም ደረጃ በመፈተሽ የበለጠ በጠነከረ መልኩ ለሕዝብ እና ለሀገር እንዲሠሩ የሚያስችል ምክክርም ይካሄዳል ብለዋል።
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ፓርቲው ከመጀመሪያው ታሪካዊ ጉባኤ በኋላ በሠራቸው ሥራዎች በሀገራችን ወቅታዊ ኹኔታዎች፣ ሀገራችን በገጠሟት ፈተናዎች እና ባሳካቻቸው ድሎች ዙሪያ በዝርዝር መወያየቱን ገልጸዋል።
ሊከናወኑ በሚገባቸው አንኳር ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል፤ ውሳኔዎችንም ወስኗል ብለዋል አቶ ይርጋ።
የዛሬው መድረክ በሁለተኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ ውሳኔዎችን ተከትሎ ጠንካራ የተግባር ሥራ ለማከናዎን ያለመ ነውም ብለዋል።
ውሳኔዎች ሀገር እና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ እንዲተገበሩ ጥልቅ ግንዛቤ እና የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በጉባኤው የተላለፉ አቅጣጫዎችን በመከተል ለሀገር እድገት እና ሰላም መሥራት ተገቢ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!