
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የደምበጫ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በዚህ ወቅት በሀገሪቱ ያጋጠመውን የደም እጥረት ለማቃለል ደም እየለገሱ ነው። እንደሀገር ያጋጠመውን የደም እጥርት ችግር ለማቃለል በከተማዋ የደም ልገሳ ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።
ዛሬ የከተማዋ ነዋሪዎች ደም በመለገስ ላይ ናቸው። ደም ሲለግስ ያገኘነው ወጣት ዓለምቀረ ሙሉ እንደገለጸው አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የደም እጥረት በመረዳት ደም ለመስጠት ተነሳስቷል። ‘‘ቆመን እየሄድን ወገኖቻችን በደም እጦት መሞት የለባቸውም፤ ለዚህም ደሜን ለመለገስ ተነሳስቻለሁ’’ ብሏል::
ሌላላው አስተያዬት ሰጭ ወጣት ደግሞ ተመሥገን ነጋ የደም እጥረት እንዳለ በተለያየ ሚዲያ መስማቱን ተናግሯል። በዚህም ‘‘በኔ ደም ሰው መዳን ስላለበት ደም ለመስጠት ተነሳስቻለሁ፤ ወደ ፊትም እለግሳለሁ’’ ነው ያለው። ሌሎች ወጣቶች ደም እንዲለግሱም ጥሪ አቅርቧል።
የደም ልገሳ ፕሮግራሙን የደምበጫ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት ማዘጋጀታቸውን ከወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡