
ባሕር ዳር:.ጥር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚቆጣጠራቸውን የትምህርት፣ የጤና፣ የወጣቶች እና ስፖርት፣ የሴቶች ሕጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ሐሳብ ሰጥተዋል። ከተነሱ ነጥቦች ውስጥም:-
👉በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መኾናቸው ያሳስባል፤ እነዚህን ተማሪዎች ለመመለስ መንግሥት ምን እየሠራ ይገኛል?
👉በክልሉ በሚገኙ የአንዳንድ ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች 12ኛ ክፍል ቢያስፈትኑም አንድም ተማሪ ያላሳለፉበት ምክንያት ሊፈተሽ ይገባል።
👉የመማሪያ መጽሐፍት ወደ ዞኖች ቢገባም ወረዳ ላይ ፍትሐዊ የስርጭት ችግር ይስተዋላል።
👉ማኀበረሰቡ የጤና መድኅን ጥቅምን አውቆ ቢመዘገብም የመድኃኒት አቅርቦት ችግር በርካቶችን ለምሬት እየዳረገ ነው።
👉የአካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች ከክልል ባለፈ በፓሪስ ፓራ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ኾነዋል። ነገር ግን
ውጤቱን የሚመጥን ሽልማት አለማግኘታቸው የተተኪዎችን ተስፋ አጉል ላይ የሚጥል ነው የሚሉት ከተነሱት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተነሱ ነጥቦች ላይም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። የትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ በርብርብ እየተሠራ ነው ብለዋል። ምዝገባውን በማስቀጠል የታለፈውን ትምህርት በማካካሻ ትምህርት ለመሸፈን እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት በተመለከተ ከወረዳ ወደ ትምህርት ቤቶች ለማድረስ በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ፈተና እንደኾነባቸው ጠቁመዋል። የ12ኛ ክፍልን የማለፍ ምጣኔ ለማሳደግም በትጋት እንደሚሠራ ወይዘሮ ኢየሩስ ተናግረዋል።
የጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በመንግሥት ጤና ተቋማት ያለውን የመድሃኒት አቅርቦት እና የስርጭት ኹኔታ በመፈተሽ የኀብረተሰብ ጤና መድኅን አገልግሎትንም መለስ ብለን በማየት ለተነሱ ጥያቄዎች መፍትሔ ይቀመጣል ነው ያሉት።
የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሠ እንደ ሀገር እና እንደ ክልል በፓራ ኦሎምፒክ ያኮሩንን አትሌቶች በክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቢሮ በኩል መሸለማቸውን ተናግረዋል።
ሰብሳቢዋ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቢሮ እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራታቸውን አመስግነዋል። የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በተለይ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደረጃውን ጠብቆ በመገንባት ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ትጋት አድንቀዋል።
ወይዘሮ አበራሽ” የትምህርት ቢሮ በጎልማሶች ትምህርት ላይ እንዳልሠራ ገልጸዋል። በሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ መምህራንን ወደ ሥራቸው መመለስ ይገባል፤ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈትም ሁሉም መረባረብ አለበት”ነው ያሉት።
ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እንዳይሠሩ ያደረጋቸው የጸጥታው ችግር ነው ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ለሰላም ሁሉም መረባረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!