
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ከሕወሀት ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ ግጭቶች እና ውጥረቶች በተማሪዎች፣ በሴቶች፣ በሕጻናት እና በሕዝቡ ላይ ያደረሱትን የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና ጫና ምን ይመስላል የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል።
ዩኒቨርሲቲው ባጠናው ጥናት ላይ ከባለ ደርሻ አካላት ጋር መክሯል። በምክክሩ ግጭቶች እና ሌሎች ችግሮች የክልሉን ሕዝብ ለከፋ ችግር ዳርገውታል ተብሏል። ከአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የመወያያ ሃሳበ ያቀረቡት አቶ አስናቀ ለውዬ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ብለዋል። ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል ነው ያሉት። ጉዳታቸው አካለዊ እና ሥነ ልቦናዊ መኾኑንም ተናግረዋል።
በተሠራው የዳሰሳ ጥናት የሴቶች እና የሕጻናት ጉዳት ከፍ ያለ መኾኑን ነው ያነሱት። በክልሉ ባለው አሁናዊ ግጭትም ሴቶች እና ሕጻናት የጉዳት ሰለባ ናቸው ብለዋል። ጉዳት የሚደርስባቸው ሴቶች እና ሕጻናትን ከጉዳት ለመጠበቅ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። ሴቶች እና ሕጻናት የሥነ ልቦና እና የሕግ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መደረጉንም ተናግረዋል። ሕጻናት እና ሴቶችን ከሥነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት። የምጣኔ ሃብት ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችም ሃብት እንዲያገኙ መሠራቱንም ተናግረዋል። ሰላም በማስፈን የሴቶችን እና ሕጻናትን ጥቃት መከላከል እንደሚገባም አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያ ለዓለም መኩሪያው ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ ባሉ ተደራራቢ ችግር ምክንያት ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል ብለዋል። በተደጋጋሚ ችግሮች ምክንያት የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ፈተና ገጥሞታል ነው ያሉት።
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ባሉ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ ከሞራል እና ከሕግ ያፈነገጡ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል ብለዋል። በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ ተማሪዎች በሥነ ልቦና እንዲጎዱ አድርጓቸዋል ነው ያሉት። በጦርነት እና በግጭት ብዙ የከፉ ነገሮችን የተመለከቱ ተማሪዎች በሥነ ልቦና ተጎድተዋል ብለዋል። ተማሪዎች ብቻ ሳይኾኑ መምህራንም የሥነ ልቦና ጫና ሰለባዎች ናቸው ነው ያሉት።
በግጭት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም፣ ቢሄዱም ምን ይደርስብናል የሚል ስጋት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ለሥነ ልቦና ጫና እየዳረጋቸው ነው ብለዋል። ተስፋ ለማድረግ፣ ለመመራመር እና አዲስ ነገር ለመፍጠር ከሥነ ልቦና ጫና መውጣት አለባቸው ነው ያሉት። ተማሪዎችን ከሥነ አዕምሮ ጤና እና ከሥነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ በቅንጅት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እና ሰላማዊ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ማስከፈት እና ትምህርታቸውን እንዱቀጥሉ ማድረግ ከሥነ ልቦና ጫና እንዲወጡ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት። ጊዜያቸውን በከንቱ እያጠፉ በሄዱ ቁጥር ለሥነ ልቦና ጫና እየተዳጉ ይሄዳሉ ብለዋል።
በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ኬዝ ስቲም አሥተባባሪ ቢረሳው ታዛየ አማራ ክልል ረጅም ጊዜ የቆዬ ግጭት፣ የወባ ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይኾን ከሱዳን የመጡ ተፈናቃዮች ሁሉ ያሉበት እና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች የደረሱበት ክልል ነው ብለዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በማኅበረሰቡ ላይ የአዕምሮ ጤና ችግር እና የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ ነው ያሉት።
ዜጎች ለአዕምሮ ጤና ችግር እየተጋለጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ግጭቱ ከቀጠለ በርካታ ወገኖች ለአዕምሮ ጤና ችግር ይጋለጣሉ ነው ያሉት። ግጭት በተራዘመ ቁጥር ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ያጣሉ፣ ከእንቅስቃሴ ይገደባሉ፣ ጫናዎች ይፈጣረሉ ይህ ሲኖር ደግሞ የአዕምሮ ጤና ችግር ይፈጠራል ብለዋል።
የአዕምሮ ጤና ችግርን ለመከላከል በትብብር መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። የአዕምሮ ጤና ችግር ማኅበረሰቡን ለከፋ ጉዳት እንደሚዳርገውም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጥ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ለአዕምሮ ጤና ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!