በኅብረተሰቡ ሕይዎት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ያለው

23

ሕገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ባስቸኳይ እንዲቆም የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱሥትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የመንግሥት ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ቀጥሏል።

ቋሚ ኮሚቴው በውሎ ውይይቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄ እና አስተያየት ካነሳላቸው ቢሮዎች ውስጥም የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ እንዲሁም የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ተጠቃሽ ናቸው።

ለቢሮዎቹ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መካከልም፦
👉 የንግድ ሥርዓቱን ማስተካከል እና የተጀመሩ ሥራዎችንም ማስቀጠል እንደሚገባ፣
👉 በጸጥታው ችግር ምክንያት የቆሙ የመንገድ ግንባታዎች እንዲቀጥሉ ቢደረግ፣
👉 ለከተማ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መስጠት እና መሠረተ ልማት ግንባታ በስፋት ሊሠራ እንደሚገባ፣
👉 የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ትኩረት ተሰጥቶት እንዲፈታ፣
👉 ከገጠር ወደ ከተማ በሚካለሉ ቀበሌዎች የወሰን ፕላን እና የመልማት ችግር እንዲስተካከል፣
👉 የቦታዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሽያጭ ክትትል እንዲደረግበት እና እንዲስተካከል፣
👉 የነዳጅ ሕገ ወጥ ሽያጭ በኅብረተሰቡ ሕይዎት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመኾኑ ትኩረት እንዲሰጠው፣ የሌሎች ምርቶችም ሕገ ወጥ ንግድ እና የምርት አቅርቦት ቁጥጥር እንዲጠናከር፣
👉 የኢንቨስትመንት ቦታ አጥረው ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሃብቶች እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣
👉 አምራች ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ወደ ገበያው እንዲያቀርቡ ድጋፍ እና ክትትል እንዲደረግ፣
👉 በሕገ ወጥ መንገድ ሃብት ማፍራት የለመደ አካል ለሰላሙ ጠንቅ ነው። የነዳጅ ሕገ ወጥ ንግድ በንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አቅም ብቻ የሚፈታ አይደለም። በተለየ ትኩረት የመንግሥትንም ሥራ ይጠይቃል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) እና የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም መሐመድ (ዶ.ር)
በቋሚ ኮሚቴው ቀርበው ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶክተር አሕመዲን በማብራሪያቸው የተሰጡ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎች እና የቋሚ ኮሚቴው ግብረ መልሶች አስተማሪ እና ገንቢ መኾናቸውን ገልጸዋል። በመልካም አሥተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ በኩል የባለሙያዎችን ክፍተት በማሻሻያ ሂደት እየሞላን እንሠራለን ብለዋል። የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ አሥተዳደር ሲካተቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመቀበል እየተፈቱ መኾኑን እና በቀጣይም በስፋት እንደሚሠራ ተናግረዋል። ችግሮችን ከተናጠል ይልቅ ግብረ ኃይል አቋቁመን በጥናት ለመፍታት እየሠራን ነው ብለዋል።

ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለው የከተማ መሬት ዘርፍን በቀጣይ ለመፍታት እና እርካታ ለማምጣት በስድስት ዘርፎች እና እስከ ተጠያቂነት የሚያደርስ ሥራም እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል። ከቀረቡ 534 የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ውስጥ 224ቱን መፈታታቸውን ጠቅሰው ሥራው አሁንም እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ቢሮ ቀርቦ የሚቆይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳይኖርም እየሠራን ነው ብለዋል።

የዲጂታላይዜሽን፣ የከንቲባ ችሎት፣ ከአሚኮ ጋር ግንኙነትን አጠናክሮ ”የአሚኮ አደባባይ” ፕሮግራምን ማስቀጠል እና የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናከር የመልካም አሥተዳደር ችግርን እንፈታለን ነው ያሉት። የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በእቅድ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው፤ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እንሠራለን ብለዋል። ፕሮጀክቶችን በወቅቱ እና በጥራት የማጠናቀቅ ጅምርን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ በተለያዩ የከተማ ሥራዎች ላይ የሚታይ ሕገ ወጥነትን ከየደረጃው አመራር ጋር ተነጋግረን እናስተካክላለን ነው ያሉት።

የኮደርስ ሥልጠናን አጠናክረን በመቀጠል የበቃ ባለሙያ ለመፍጠር እየሠራን ነው ሲሉም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማትን የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾን እንሠራለን፤ ኅብረተሰቡም በልማቱ ደስተኛ ነው ብለዋል።

የከተማ ቤት ልማት ሥራ ችግር ፈቺ አይደለም የተባለው ትክክል ነው፤ ችግሩን ለመፍታት ስትራተጂ እና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። በዚህም ባለሃብቶች በልማቱ እንዲሳተፉ የማድረግ እቅድ መዘጋጀቱንም ነው ዶክተር አሕመዲን የገለጹት።

ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረን በጋራ እንሠራለን ብለዋል።

የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ኢብራሂም መሀመድ (ዶ.ር) በሰጡት ምላሽ ቢሮው የተሰጡት አስተያየቶችን በግብዓትነት ይዞ እንደሚሠራባቸው ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እና የኑሮ ውድነትንም ለማረጋጋት የአደረጃጀቶችን አቅም አሟጦ በመጠቀም እንደተሠራ ገልጸዋል። 17 የክልል ተቋማትን ያካተተ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በኦንላይን አገልግሎት የንግድ ፈቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ መሰረዝ እና መሰል ሥራዎች የአገልግሎት ማዕከሎችን ችግር በመፍታት ለመሥራት እንደተቻለ አመላክተዋል።

የኢንተርኔት ችግር ባለባቸው ወረዳዎች ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ያለቅጣት የሚያድሱበት ጊዜ በመስጠት እንዳይቀጡ መደረጉንም ተናግረዋል።

በሕገ ወጥ መንገድ እና በአቋራጭ ለመክበር የሚደረገው እንቅስቃሴ ሕዝቡን እንደሚጎዳ ተረድተን በትኩረት እየሠራን ነው ሲሉም ተናግረዋል። ሕገ ወጥነትን በመከላከል በኩል 55 ሺህ ነጋዎች በሕገ ወጥነት ተይዘው ለማስተካከል እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በጸጥታው ችግር ምክንያት በየቦታው ያለው ዝርፊያም አቅርቦትን እንዳስተጓጎለ ያነሱት ዶክተር ኢብራሒም የመረጃ እጥረትም እንዳለ አንስተዋል።

የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ በቀጣይ እንደሚሠራም ተናግረዋል። አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ግንባታ ጥያቄዎች ለሕገ ወጥ ንግድ የታሰቡ መኾናቸውን የጠቀሱት ኀላፊው ነገር ግን በተጨባጭ የነዳጅ ማደያ የሌላቸው ወረዳዎች በቀጣይ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ዶክተር ኢብራሂም የናፍጣ እጥረት አለመኖሩን ተናግረዋል። ቤንዚን ለመስኖ ማጠጫ ሞተር ተፈላጊ መኾኑ፣ የአንዳንድ ማደያዎች ሕገ ወጥ ሽያጭ እና በሕገ ወጥ የቤንዚን ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለተሽከርካሪዎች መኖራቸው እጥረቱን አባብሰውታል ብለዋል። ኾኖም በጠንካራ ክትትል እና ቁጥጥር በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ገልጸዋል። የክልል ቢሮዎችም የነዳጅ አጠቃቀማቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቢሮው በቀጣይም ክትትል፣ ቁጥጥር እና እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው ድጋፍም እንደሚያስፈልገው ዶክተር ኢብራሒም አንስተዋል።

ገበያ ለማረጋጋትም የምርት ትሥሥር በማድረግ፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ዋጋ በማሳወቅ እየተሠራ ነው። የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባሕል የዳበረ ባለመኾኑ ለኑሮ ውድነት እያጋለጠ መኾኑንም አንስተዋል። የግብርና ምርቶችን ለኢንዱስትሪዎች የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል ዶክተር ኢብራሒም።

የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቀን እንገነዘባለን፤ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በግብርናው ምርት ዋጋ የመቀነስ አዝማሚያ፤ በኢንዱስትሪው ደግሞ ከፊሉ የመቀነስ አዝማሚያ ታይቷል፤ ከፊሉ ደግሞ ባለበት ነው ብለዋል። በቀጣይም በተሟላ ጥናት አስፈላጊው ሥራ እና እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የዶክተር አንዷለም ዳኜ ቤተሰቦች ሊደገፉ በሚችሉባቸው ኹኔታዎች ውሳኔ አሳለፈ።
Next articleየሕግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ መኾናቸውን የአድማ መከላከል እና መደበኛ ምልምል ሠልጣኞች ተናገሩ፡፡