
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ዶክተር አንዷለም ዳኘን ህልፈት ተከትሎ መሠራት ባለባቸው ተግባራት ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ዩኒቨርሲቲው የዶክተር አንዷለም ዳኘን ህልፈት ተከትሎ መሠራት ባለባቸው ሥራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን በተለይ ቤተሰቦቹ ሊደገፉ በሚችሉባቸው እና በሕይዎት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ልዩ ሙያዊ አስተዋጽኦዎችን መዘከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
ዶክተር አንዷለም የተሰጣቸውን ጸጋ ሳይሰስቱ በመጠቀም ለበርካቶች የዘርፉ ባለሙያዎች እና በሙያው ላገለገሏቸው በርካታ ህሙማን የቅን አገልጋይነት ተምሳሌት የነበሩ እንቁ ባለሙያ ነበሩ። ገና በ37 ዓመታቸው ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው። ህጻናት ልጆችን ትተው ያለፍ እና ቤትም ሆነ ሌላ ንብረት የሌላቸው ናቸው።
የቀረበላቸውን በርካታ ዓለም አቀፍ የሥራ ቅጥር ግብዣዎች ባለመቀበል ወገናቸውን ለማገልገል ቆርጠው ነበሩ። በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀዶ ጥገና ክፍል የነበራቸውን ልዩ አበርክቶ እና የቀዶ ጥገና ክፍሉን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሻሻል እየጣሩ የነበረ እና እውን ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሰው ያለፍ ናቸው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የነበረውን ሞያዊ አቅም ተጠቅመው ራሳቸውን ለተገልጋዮች በቅንነት ሰጥተው ያለፍ ታላቅ ባለሙያ እንደነበሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው እና አገልግሎቱን ያገኙ ደምበኞቻቸው የሚመሰክሩላቸው ድንቅ ሀኪም የነበሩ መኾኑን ዩኒቨርሲቲው በጥልቀት አይቷል፡፡
በመሆኑም የዶክተር አንዷለም ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ሲደርሱ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በነጻ እንዲማሩ፤ ባለቤታቸው ከትምህርት ዝግጅት አንጻር በሲቪል ምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪ ያላት እና ጥሩ ዓቅም ያላቸው በመኾናቸው በዩኒቨርሲቲው የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የሚቀጠሩበት ኹኔታ እንዲመቻች፤ ዶክተር እንዷለም በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታሪክ የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና የሠሩት እርሳቸው ናቸው።
ክፍሉን እስከ ህልፈታቸው ድረስ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ በመኾኑ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ዋርድ በስማቸው ዶክተር አንዷለም ዳኘ ቀዶ ጥገና ዋርድ ተብሎ እንዲሰየም ተወስኗል። የአንዷለምን የአገልጋይነት ጥግ እንዲሁም ለሙያው የተሰጠ ተምሳሌታዊነትን በቋሚነት ለመዘከር እና ማስተማሪያ እንዲሆን በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ሃውልት እንዲቆምላቸው፤ በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ School of Medicine ውስጥ በስማቸው BDU Talent Scholarship እንዲቋቋም ተወስኗል።
ለ40ኛ ቀናቸው መታሰቢያ የሚደርስ ስለ ዶክተር አንዷለም የሕይወት ታሪክ የሚዳስስ መጣጥፍ እንዲዘጋጅ ተወስኗል። ይህ ውሳኔም በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እና በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይሁንታን አግኝቶ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡ ተግባሩን ለማሳለጥ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ በኩል የሚሠሩ ዝርዝር ሥራዎችን የሚከታተል የሥራ ባልደረቦቻቸውን ያቀፈ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡
በመጨረሻም የአንዷለም ዳኘን(ዶ.ር) የግፍ ግድያ አስመልክቶ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም ፍትሕን አጥብቆ የሚሻ ሲሆን ክስተቱ የአንድ ጊዜ አጋጣሚ ብቻም ሳይሆን ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ያጣውን በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ አገልግሎት ኀላፊ አድነው በለጠን ጨምሮ እየተደጋገመ የመጣ እና ለሕብረተሰቡ አገልጋይ የሆኑ እንቁ ሃኪሞቻችንን ደህንነት እንዲሁም የማሕበረሰቡን የጤና አገልግሎት በእጅጉ እየተፈታተነ ያለ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ተገቢውን እና ጥልቅ ምርመራ አድርገው በግድያው ላይ እጃቸው ያለበትን አካላት በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡ ተጠይቋል።
ይህ ጉዳይ በቋሚነት መፍትሔ በሚያገኝበት መንገድ ላይ ዩኒቨርሲቲው በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶች እንደሚደረግም ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!