“በችግር ውስጥ ላለው ማኅበረሰብ የአዕምሮ ጤና እና የማኅበረሰባዊ የሥነ ልቦና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል” ሙሉነሽ አበበ (ዶ.ር)

41

ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ከሕወሓት ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ ግጭቶች እና ውጥረቶች በተማሪዎች፣ በሴቶች በሕጻናት እና በመላ ሕዝቡ ያደረሰውን የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና ጫና ምን ይመስላል የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል።

ዩኒቨርሲቲው ባጠናው ጥናት ላይ ከባለ ደርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። በምክክሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ መምህርት ሙሉነሽ አበበ (ዶ.ር) የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ የቀጠለው ችግር ማብቂያ የሌለው ኾኖ ቀጥሏል ብለዋል። ከ2012 ዓ.ም ወዲህ በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ አውዳሚ ጦርነት እና የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት መከሰቱን ገልጸዋል። በማኀበረሰቡ ግጭት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ሞት፣ የቤተሰብ መበተን፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ውድመት ደርሷል ነው ያሉት።

በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ውድ የኾነው የሰው ሕይወት ጠፍቷል ብለዋል። የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የሰብዓዊነት መሠረት የኾኑ እሴቶቻችን ውድመት ደርሶባቸዋል ያሉት መምህርቷ በመላ ማኅበረሰቡ ዘንድ ያስከተለው እና እያስከተለው ያለው የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ከባድ ነው ብለዋል።

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት አረመኔነት፣ እብሪት፣ ድፍረት፣ ጭካኔ እና ሌሎች ከሰብዓዊነት የወጡ ድርጊቶች ንጹሐንን ለአሰቃቂ ጉዳት እየዳረጋቸው መኾኑን አንስተዋል። እየደረሰ ያለው የአዕምሮ ጤና መቃወስ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።

ጦርነት እና ግጭት፣ ልጓም የሌለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ የኑሮ ውድነት፣ የትምህርት መቋረጥ፣ ዝርፊያ፣ እገታ እና ሌሎች ችግሮች ማኅበረሰቡን ለአዕምሮ ጤና መታወክ እና ለሥነ ልቦና ችግር እየዳረጉት ነው ብለዋል። በዚህ ወቅት በመላ ማኅበረሰቡ ችግር እየደረሰ መኾኑንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ የሚከበር እና የሚታፈር ሰው፣ መሪ፣ ተቋም፣ የማይዘበትበት እሴት፣ ሃይማኖት አይገኝም ነው ያሉት። ሁላችንም የማይነጉ የሚመስሉ ሌሊቶችን፣ የከበዱ ጭንቀቶችን፣ ውጥረቶችን አሳልፈናል፣ አሁንም በድብርት እና በጭንቀት ውስጥ ነን ነው ያሉት።

በሕዝብ ላይ እየተፈራረቀ የተከሰተው ችግር ስፋት እና ጥልቀት ማኅበረሰቡ ጠንካራ ኾኖ እንጂ የሚቻል አለመኾኑንም አንስተዋል። በዚህ ወቅት ለአዕምሮ ጤና እና ለሥነ ልቦና ልዩ ትኩረት ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። በችግር ውስጥ ላለው ማኅበረሰብ የአዕምሮ ጤና እና የማኅበረሰባዊ የሥነ ልቦና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል።

ባለድርሻ አካላት ዕውቀት እና ሀብታቸውን አቀናጅተው መሥራት አለባቸው ነው ያሉት። በዚህ ወቅት በጋራ መሥራት አስፈላጊ ነው፤ በጋራ አለመሥራት የሞራል ውድቀት ያስከትላል ነው ያሉት። በሥነ አዕምሮ ጤና እና በማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ላይ አለመሥራት እንደተማረ ሰው ውድቀት ነው ብለዋል። ተማረ የተባለው አካል ለሕዝቡ ሊደርስለት ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ላይ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የሥነ ልቦና ጫና ያልደረሰበት አለመኖሩንም አንስተዋል። ምርምር በማድረግ እና በማስረጃ የተደገፈ የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ከችግሩ መውጣት ይገባል ነው ያሉት። ችግሩን በቅንጅት እና በመናበብ መፍታት ይጠበቃልም ብለዋል።

የኢትዮጵያዊነት መሠረት የኾኑ ወርቃማ እሴቶችን እና የማኅበረሰቡን የጥንካሬ መሠረቶች ማዳን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክር ቤቱ የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ።
Next articleባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የዶክተር አንዷለም ዳኜ ቤተሰቦች ሊደገፉ በሚችሉባቸው ኹኔታዎች ውሳኔ አሳለፈ።