
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ18ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግሥቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ረቂቅ አዋጁ ነጻ እና ገለልተኛ የኾነ እና አደረጃጀቱ ከተጽዕኖ የጸዳ የሕግ እና ፍትህ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ጠንካራ የዳኝነትና የፍትህ ተቋማት ለመፍጠር የሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ተጠሪነት ማሻሻል አስፈላጊ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረገ ጥናትና ምርምር በማድረግ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን እንዲሁም ሕጎችን ከወቅታዊ የዓለም እና የሀገሪቱ የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ ጠንካራ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ እንደገና መቋቋሙ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ታአማኒና ቀልጠፋ አገልግሎት ለመስጠት ያሚያስችሉ የሕግ ሙያተኞች ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ ቀድመ ስልጠና የሚለው በስራ ላይ ሂደት የፍትህ ባለሙያዎችን እያበቁ መሄድ ቢቻል፣ በየቦታው የስልጠና መዕከል ከመክፈት ይልቅ በማዕከል በማድረግ ዘርፉን መደገፍ ቢቻል የሚል አስተያየት የምክር ቤት አባላት ሰጥተዋል፡፡
ከቅድመ ስልጠና ጋር በተያያዘ የፍትህ ባለሙያዎች ዳኞች እና ዐቃቢያን ህጎች በሰዎች ንብረት እና ህይወት ላይ ለሚወስኑት ውሳኔ በእውቅትና እና በክህሎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የቅድመ ስልጠና አስፈላጊ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ አስረድተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በህግ ጉዳዮች ጥናት እና ምርምር በማድረግ እና ፖሊሲዎችን በማመንጨት እንደሀገር በፍትህ ሥርዓቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለማረም እንደሚያግዝ አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ አስረድተዋል፡፡ ኢንስቲትዩት ለፍትህ ሚኒስቴር ከነበረበት ተጠሪነት ወጥቶ፤ በአሁኑ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ መሆኑን በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል፡፡
ምክር ቤቱ የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1369/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን የምክርቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!