“በዜጎች ሥነ አዕምሮ እና የሥነ ልቦና ዙሪያ መምከር አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)

32

ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ከሕወሓት ጦርነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ ግጭቶች እና ውጥረቶች በተማሪዎች፣ በሴቶች በሕጻናት እና በመላ ሕዝቡ ያደረሱትን የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና ጫና ምን ይመስላል የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል።

ዩኒቨርሲቲው ባጠናው ጥናት ላይ ከባለ ደርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። በምክክሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ግጭቶች እና መፈናቀሎች ማኅበረሰቡን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት እንዲጋለጥ አድርገውታል ብለዋል።

ችግሩ እንደ ሀገር መኾኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በአማራ ክልል ግን የባሰ መኾኑን ነው ያመላከቱት። ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫናው ሕዝብን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ መኾኑንም ገልጸዋል። እንደ ሀገር ያሉ አለመረጋጋቶች ግጭቶች እና አሳሳቢ ቀውሶች ማኅበረሰቡን ለከፋ ችግር እየዳረጉት ነው ብለዋል። በተለይም ሕጻናት፣ ታዳጊዎች እና ሴቶች የችግሩ ሰለባ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

በግጭት፣ በመፈናቀል፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሀብቶች ውድመት ምክንያት የሚፈጠረውን ስር የሰደደ የአዕምሮ ጤና ችግሮችን መፍታት ግድ ይላል ነው ያሉት። ጦርነቱ ሥነ ልቦናዊ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ግጭት የሚያደርሰው አካላዊ ውድመት ካለፈ በኋላም የማይታዩ ቁስሎችን ትቶ ያልፋል ነው ያሉት።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ግጭት፣ ጭንቀት እና የሥነልቦናዊ ጉዳት መፍትሔ ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል። ለችግሮቹ አስቸኳይ መፍትሔ ማበጀት ካልተቻለ በስተቀር የግለሰብ ደኅንነትን ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር የማኅበራዊ መረጋጋት እንዳይኖር እና ምጣኔ ሀብቱ እንዳያገግም ያደርጋል ብለዋል።

የአዕምሮ ጤና የሰላም ግንባታ እና የሀገር ዕድገት ማዕከላዊ ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። ማኅበረሰቡ ከችግር እንዲያገግም ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የአዕምሮ ጤናን ችላ ማለት ልማትን እና ሌሎች ጥረቶችን ሁሉ ይጎዳል ብለዋል። በዜጎች ሥነ አዕምሮ እና ሥነ ልቦና ዙሪያ መምከር አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር ሙያዊ ውይይት ማዳበር ያስፈልጋልም ነው ያሉት። ምክክሩ በአማራ ክልል ለአደጋ ተጋላጭ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስላለባቸው አዕምሮአዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ግንዛቤ ይፈጥራል ብለዋል። ክፍተቶችን መለየት እና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማስቀመጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የሙያ ማኅበራት በክልሉ ያለውን ችግር በምርምር በመታገዝ የመፍታት ሚና እንዳላቸውም አመላክተዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል። የተቀናጀ የአዕምሮ ጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት፣ ተጽዕኖ የሚፈጥር ምርምር ለማካሄድ እና በችግር ጊዜ ውስጥ በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ የመፍትሔ አማራጮችን ለማመላከት ዝግጁ መኾኑን ነው ያነሱት።

ሌሎች ተቋማትም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሠሩ አሳስበዋል።አሁን የተደረገው ጥናት ገና ጅምር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በሀገራችን ያለውን የአዕምሮ ጤና ችግር ለመቅረፍ የበለጠ መሥራት እና በፍጥነት መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል። የአዕምሮ ጤና ላይ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ጥናቱ ቀጣይነት ያለው እና ለሥነ አዕምሮ እና ለሥነ ልቦና ደኅንነት መሠረት የሚጥል መኾን አለበትም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ጎንደር ውበቷ ታድሷል” ጫልቱ ሳኒ
Next articleምክር ቤቱ የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ።