
ጎንደር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በጎንደር ከተማ እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እየተመለከቱ ነው። ከሚንስትሯ በተጨማሪ ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የሥራ ኀላፊዎች ጎንደር ከተማ ገብተው የመሰረተ ልማቶችን አፈጻጸም እየጎበኙ ይገኛሉ።
የሥራ ኀላፊዎች የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትና የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳትን ጎብኝተዋል። የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት፣ አንድነት የተገነባበት ድንቅ ቅርስ መኾኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል። የበርካታ ዓመታት ታሪክ ያለው አስደናቂ የኪነ ሕንጻ ግንባታ አይተናል ያሉት ሚኒስትሯ አባቶቻችን አሻራቸውን አስቀምጠው የይቻላል መንፈስን ለትውልዱ አስተምረውናል ብለዋል።
አብያተ መንግሥታቱ ለበርካታ ዓመታት ተዘንግቶ ወደ መፍረስ ተቃርቦ ነበር፤ ዛሬ ላይ የሚመጥነውን እድሳት አግኝቷል ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ቅርስ የሀገራችንን የይቻላል መንፈስ ያሳየ ነው ያሉት ሚኒስትሯ የራሳችንን ታሪክ በራሳችን መጠበቅና መንከባከብ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል። የትውልድን ቅብብሎሽ ያሳየንበትና አንድነትን የገነባንበት ድንቅ ቅርሳችን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከቅርሱ ጋር ተያይዞ በከተማዋ የተሠራው የኮሪደር ልማት ለቅርሱ ድንቅ ውበት መኾኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ በመጎብኘታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። በቅርሱ አካባቢ የሚገኙ ለከተማዋ የማይመጥኑ ሕንጻዎች ተነስተው ከተማዋን የሚመጥናት ግንባታ በመከናወኑ ጎንደር ውበቷ ታድሷል ብለዋል ሚንስትሯ።
የጎንደር – አዘዞ አስፖልት መንገድ የኅብረተሰቡ የዓመታት ጥያቄ በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ አሁን ላይ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ እየደረሰ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ከኮሪደር ልማቱ ያገኘነው ልምድ በመኖሩ በቀጣይ ሌሎች ሥራዎችም በተገቢው መንገድ እንዲከናወኑ የምንሠራ ይሆናል ብለዋል።
አሁን የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል እንሠራለን፤ ማኅበረሰቡ ልማት ወዳድ በመኾኑ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። በቀጣይ ከፒያሳ – ኮሌጅ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በማስቀጠል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ቦታ ማጽዳትና ለሥራ ምቹ የማድረግ ተግባር መከናወኑን አንስተዋል።
ያለሕዝብ ድጋፍ የሚከናወን የልማት ተግባር ባለመኖሩ ማኅበረሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!