
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚቆጣጠራቸውን የትምህርት፣ የጤና፣ የወጣቶች እና ስፖርት፣ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮዎችን እንዲሁም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል። የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) በክልሉ የሴት ልጅ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል ብለዋል። ጥቃቱን ለመቀነስ ቢሮው እያደረገ ያለውን ሥራም ጠይቀዋል።
በኀብረተሰቡ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት እንደሚገባም ዶክተር ደሴ አሳስበዋል። በሴት ልጆች ላይ ጥቃት የፈጸሙትን አጥፊዎች ተከታትሎ ለፍትሕ በማቅረብ ረገድ ቢሮው ውስንነት ታይቶበታል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎችም አሉ። የፊተኞቹ ወንጀለኞች ለሕግ ካልቀረቡ ጥቃቱ ይባባሳልና ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ሊሠራ ይገባዋል ነው ያሉት።
የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ከፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው ብለዋል። ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወንጀለኛን አሳዶ ለመያዝ አስቸጋሪ ኹኔታ ፈጥሮብናል ነው ያሉት።
የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ በበኩላቸው ስለመሥሪያ ቤታቸው ሲናገሩ ሁሉንም የመገናኛ አውታሮች በመጠቀም ለኀብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ስርጸት ተሠርቷል ነው ያሉት።
ከተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመሥራታቸውም ከ200 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች የምሥክር ወረቀት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን