
ደብረ ብርሃን: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ ምክር ቤት የ4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 44ኛ መደበኛ ጉባኤ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው። በጉባኤውም በከተማው የሚገኙ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መንግሥቱ ቤተ ምክር ቤቱ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡ ተቋማት በበጀት ዓመቱ እንዲያከናውኑ የሚጠበቁባቸውን ተልዕኮዎች እንዲወጡ ምክር ቤቱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ያለፉ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ከተማው በርካታ የልማት እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተከናወኑበት መኾኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል፡፡ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 120 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት ወራት በከተማዋ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና በሕገ ወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱት ላይ ርምጃዎች መወሰዳቸውን አቶ በድሉ ገልጸዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ከ3ሺህ በላይ የሚኾኑ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷልም ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1ሺ 300 ነጋዴዎች የታገዱ ሲኾን ሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እና አሥተዳደራዊ ርምጃዎች ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት በሪፖርታቸው።
ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ ለማዘዋወር የሚደረገውን ጥረት ለመግታትም በተከናወነው ተግባር ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መወረሱም ተገልጿል፡፡ ከ890 በላይ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ማስቆም እና ቦታውንም ወደ መሬት ባንክ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡ የገበያ ማረጋጋት ሥራን በተመለከተ በግብርና ምርት 45 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶች መቅረባቸውም ተጠቁሟል፡፡
ሸማች ማኅበራትን በማቋቋም፣ ነባሮቹን የማጠናከር እና የካፒታል መጠናቸውን በማሳደግ ድጋፍ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በከተማ አሥተዳደሩ ከ11ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ እና ነገ በሚያደርገው ውይይት ባለፉት ወራት የተቋማት እንቅስቃሴን ገምግሞ በቀጣይ ወራት መሠራት ባለባቸው ተልዕኮዎች ዙሪያ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን