መንገዶች በጋ ከክረምት እንዲያገለግሉ ኾነው እየተገነቡ ነው።

42

ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እንደቀጠለ ነው። ተግባራቸው እየታዩ ካሉት ተቋማት ውስጥ የክልሉ መንገድ ቢሮ አንዱ ነው።

የተቋሙን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴዎቹ ያቀረቡት የቢሮ ኀላፊው ጋሻው አወቀ ( ዶ.ር) ናቸው። ኀላፊው በ2016 በጀት ዓመት የነበረውን 32 ሺህ 523 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን ወደ 34 ሺህ 572 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ለማሳደግ ታስቦ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ በሪፖርታቸው አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ 2ሺህ 48 በላይ ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የታሰበ ሲኾን ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ አፈጻጸም እንደነበር አንስተዋል። መንገዶች በጋ ከክረምት እንዲያገለግሉ እና ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ኀላፊው አመላክተዋል። የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት እንደ ክልል ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።

ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች እንደሚገኙበትም በሪፖርታቸው አብራርተዋል። በዚህ ዓመት የፌዴራል ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር 760 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታስቦ በመከናወን ላይ ነውም ብለዋል። ቢሮው አሠራሩን ለማሻሻል ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን እና የሪፎርም ሥራዎችን ለማከናወን ጥረት እያደረጉ እንደኾነም ገልጸዋል።

የአሚኮየአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢንዱሥትሪ እና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት ሥራ እየገመገመ ነው።
Next articleሰውን ተክቶ የሚሠራው አዲስ ቴክኖሎጂ!