
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል። የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ ለኀብረተሰቡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ለመኾን እየሠራ ይገኛል።
አገልግሎቱ ከቀበሌ እስከ ክልል ባለው መዋቅር ተደራሽ እንዲኾን ለባለድርሻ አካላት ሥልጠና መሰጠቱንም ኀላፊዋ ተናግረዋል። በክልሉ በሁሉም ዞኖች ጥራት ያለው መረጃ በማመንጨት ለሚመለከተው አካል ሙሉ የኾነ ተዓማኒ መረጃ እየሰጠ ነውም ብለዋል። ኀላፊዋ እንደ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ወጣቶች እና ስፖርት፣ ትምህርት እና ጤና ቢሮ ካሉ ተቋማት ጋር በመናበብ እየሠሩ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት።
ከባለፈው ስድስት ወራት ቀደም ብሎ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ተጠቃሚ አልነበሩም ያሉት ወይዘሪት መዓዛ አሁን ግን በተዘረጋው ቅንጅታዊ አሠራር አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል። ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች የወሳኝ ኩነት ክበባትን እንዲያቋቁሙ መደረጉንም ኀላፊዋ አብራርተዋል።
ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር መንገዶች ሲዘጉ እንደ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት በርካታ ችግሮች ገጥመውናል ያሉት ወይዘሪት መዓዛ በችግሩ ተደናቅፈው ሳይወድቁ ይልቁንም በአደረጃጀት ተጠናክረው የልደት፣ የጋብቻ ፣ የጉዲፍቻ እና የሞት ኹነቶች ሳይቋረጡ በመመዝገብ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የተመዘገበው ከ98 በመቶ በላይ የኀብረተሰብ ክፍል በወቅቱ ማስረጃውን ወስዶ እየተጠቀመበት መኾኑን ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!