
ሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የመስኖ ልማቶችን ተመልክተዋል።
በወረዳው ከ1ሺ 500 በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ ተሸፍኗል። 1መቶ 43 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በዚህ የመስኖ ወቅት እንቅስቃሴም ከ4ሺ 400 በላይ አርሶ አደሮች ጥቅል ጎመን፣ ድንች፣ ምስርና ሌሎንም እያመረቱ ነው።
የወረዳው አርሶ አደሮች እንዳሉት የእርሻ ማሳቸውን በመስኖ በማልማት በሄክታር ከሚያገኙት እስከ 1 ሚሊዮን ብር መሸጥ ችለዋል። የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ሐሳብ በመተግበር በመስመር ከመዝራት ጀምሮ የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን መከተላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ መስኖን በመጠቀም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ነው ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በመንቀሳቀስ የመስኖ ልማት ላይ የሚያጋጥሙ የገበያ ትሰስርና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነበር።
ርእሰ መስተዳድሩ በሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ተገኝተውም በከተማው የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁስን የማምረት ሂደትም ተመልክተዋል። በባለሀብት እየለማ ያለ የማንጎ እርሻ ኢንቨስትመንትንም ጎብኝተዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ፈረደ ውኃ ችግኝ ጣቢያ እየተባዛ የሚገኘውን የችግኝ ልማትንም ጎብኝተዋል። በችግኝ ጣቢያው አፕል፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ፓፓያና ብርቱካን ችግኞች ለአልሚ አርሶ አደሮች ለማራጨት እየለሙ ነው።
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ