
ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ በአካባቢው የብረት፣ የወርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የሴራሚክ፣ የግራናይት እና የኖራ ማዕድናት በስፋት መኖራቸው በጥናት ተረጋግጧል ብሏል፡፡ ኾኖም እነዚህ የከበሩ ማዕድናት ለምተው ለሀገራዊ ልማት አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ በየዓመቱ የማይፈቱ ችግሮች እንቅፋት ኾነዋል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አበባው መኮንን የክልሉ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባካሄዱት የማዕድን ፍለጋ ጥናት በመጠን እና በቦታ በርካታ ማዕድናት መኖራቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡ የማዕድን ጸጋዎቹ እንዲለዩ መደረጋቸው የሚመሠገን ነው ያሉት ኀላፊው ኾኖም እነዚህን ጸጋዎች አልምቶ ሀገራዊ አቅም ማድረግ ግን አልተቻለም ነው ያሉት፡፡
እነዚህ የከበሩ ማዕድናት አንዳንዶቹ እስከ 300 ዓመታት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አቅም ያላቸው ሲኾን በጥራታቸውም እጅግ ተመራጮች መኾናቸው ስለመረጋገጡ ነው ያብራሩት፡፡ እነዚህ ጸጋዎች የሥራ ዕድል ምንጭ፣ የኢኮኖሚ ዋልታ፣ አዲስ ገበያ መፍጠርያ አቅም እንዳይኾኑ በቅድሚያ መሠራት የሚገባቸው የመንገድ መሠረተ ልማት እና የኀይል አቅርቦት እጥረቶች መኖር ችግሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡
የበርካታ ባለሀብቶች ጥያቄም እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲመለሱ መጠየቅ ነው ያሉት ኀላፊው ኾኖም እነዚህ ማዕድናት ከጥናት እና ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውጭ ወደ ሥራ የገቡ የሉም ነው ያሉት፡፡ አንዳንድ ማዕድናት ላይ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ሲኾኑ ወርቅን በተመለከተ አበርገሌ ላይ ወጣቶች በባሕላዊ መንገድ ተደራጅተው እንዲሠሩ የማመቻቸት ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
አቶ አበባው የክልሉ መንግሥት ባመቻቸው መሠረት ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጨማሪ የማዕድናት ጥናት እና የተገኙ ማዕድናት አቅም ስፋት እና መጠን ላይ ዘንድሮም በ15 ቀበሌዎች ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት። የፌዴራል መንግሥት ባለሙያዎች በቅርቡ ጥናት አድርገው ተመልሰዋል፤ በቀጣይም በተደራጀ መንገድ በመመለስ ተጨማሪ አቅምን ለማውጣት እንደሚሠሩም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በዝቋላ፣ በአበርገሌ፣ በሰቆጣ፣ በጋዝጊብላ ወረዳዎች እና በሰቆጣ ከተማ በስፋት ማዕድናት ያሉባቸው እንደኾነ በጥናቶቹ ስለመለየታቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አቻሙ ሞገስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!