በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማኝናውንም ዓይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ማስነሳትም ኾነ ማብረር እንደማይቻል ተገለጸ፡፡

85

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚደረግ የድሮን እና ሌሎች በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1276/2014 በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን የማስጠበቅ ኀላፊነት አለበት።

ተቋሙ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን ስጋቶች ለመከላከል የሚያስችል በቂ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ዝግጅት አድርጓል። ሥራው ውጤታማ እንዲኾንም ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ጠንካራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚፈልግ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በተለይ ከመጪው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ቅንጅቱን ማጠናከር አስፈላጊ በመኾኑ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማኝናውም ዓይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ፈቃድ ማስነሳትም ኾነ ማብረር እንደማይቻል መግለጫው አመልክቷል፡፡

በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም አስፈላጊ ከኾነ ጠያቂው አካል የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን ዓይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ አስቀድሞ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን መጠየቅ እና ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ መግለጫው አስታውቋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዘፈቀደ የሚኒሱ እና የሚበሩ ድሮኖች ካሉ ተቋሙ አዲስ አበባን እና ዙሪያዋን በጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ ያጠረ በመኾኑ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ ድሮኖቹን ከአየር ላይ በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የድሮን አብራሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ከሥራ ጋር በተያያዘ ድሮኖችን መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም አካል በ+251 983 00 02 98 እና +251 983 00 04 01 ስልክ ቁጥሮች በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችል በመግለጫው አሳስቧል።

Previous article“ውብ ከተሞች የሰው ልጆች የሥራ ውጤቶች ናቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የደረጃ ማሻሻያ ግንባታ በጥራት እና በፍጥነት እየተከናወነ ነው።