“ውብ ከተሞች የሰው ልጆች የሥራ ውጤቶች ናቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

46

ባሕር ዳር: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸው እየተገመገሙ ካሉት ቢሮዎች ውስጥ አንዱ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የቢሮውን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴዎች አቅርበዋል። “ውብ ከተሞች የሰው ልጆች የሥራ ውጤቶች ናቸው” ያሉት ኀላፊው መልካም ነገር ከሠራን ጥሩ ከተሞችን እናያለን ካልኾነ ደግሞ በተቃራኒው ነው ብለዋል። ባለፉት ጊዜያት ከላይ እስከ ታች ድረስ ባሉ ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ እና አሠራርን ማክበር ላይ የሚስተዋሉ ፈተናዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። ባሳለፍናቸው ስድስት ወራት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት አድርገናል ነው ያሉት።

በተሠራው ሥራም ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት ኀላፊው። ለአብነትም ቢሮ ድረስ መጥተው የሚጉላሉ ደንበኞች እንዳይኖሩ በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል። ሕገ ወጥ የቤቶች ግንባታ ሌላው ችግር እንደኾነም ተናግረዋል። ብልሹ አሠራሮች እንዳይኖሩ ቢሮው አበክሮ እየሠራ እንደኾነ አብራርተዋል። በተደረገው ክትትልም መልካም ባልኾነ አሠራር ላይ በተሳተፉ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ እርምት መወሰዱንም አንስተዋል።

የከንቲባ ችሎት እና አሚኮ አደባባይ ፕሮግራሞች ሰዎች ቅሬታቸውን እና እንግልታቸውን የሚያወጡባቸው አሠራሮች ናቸው ያሉት ኀላፊው በበጎ ሊነሱ የሚገቡ በመኾናቸው በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እና ሳቢ እንዲኾኑ እየተሠራ ያለው ተግባርም ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል።

በከተሞች አካባቢ ያለው የመሠረተ ልማት ሽፋን ላይ በትኩረት የተሠራ ቢኾንም አሁንም የሚቀሩ ተግባራት እንዳሉ አመላክተዋል። ከ2016 ዓ.ም ወደ 2017 ዓ.ም የተዛወሩ 102 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የነበሩ ቢኾንም 93 ያህሎቹን ማጠናቀቅ እንደተቻለ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ተኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባት እና የመጠገን ተግባር አንዱ እንደነበር ገልጸዋል። አመርቂ ተግባራት የተሠራበት ወቅት ነበርም ብለዋል። የከተማ ቦታ አሰጣጥን በተመለከተ መሬትን እየሸነሸኑ ከመስጠት ይልቅ ማኅበራት ወደ ላይ እየገነቡ ተጠቃሚ የሚኾኑበት መንገድ እየተጀመረ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ከተሞች ውብ፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እና ከብልሹ አሠራር የጸዱ እንዲኾኑ በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካል ሚና ሊኖር እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበክልሉ የማዕድን ላቦራቶሪ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው።
Next articleበአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ማኝናውንም ዓይነት ድሮን ያለ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ፈቃድ ማስነሳትም ኾነ ማብረር እንደማይቻል ተገለጸ፡፡