
ባሕር ዳር: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ የቢሮውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል። ክልሉ በርካታ የማዕድን ጸጋ ያለበት መኾኑንም አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑም አመላክተዋል። የሥነ ምድር ጥናት ማካሄድ እና የማዕድን ልማት ቀጣና ልየታ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲከወኑ የቆዩ ተግባራት መኾናቸውን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። በማዕድን ዘርፍ ክልሉ ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም የማዕድን ላቦራቶሪ መኖር አለበት ያሉት ኀላፊው ይህ አለመኖሩ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
በቀጣይ በክልሉ የማዕድን ላቦራቶሪ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። የወርቅ ምርትን ለማዕከላዊ ገበያ በመላክ በኩልም ባለፉት ስድስት ወራት በትኩረት የተሠራ ተግባር እንደነበር አንስተዋል። የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በኩልም የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ድርሻውን ሲወጣ እንደቆየም አቶ ኃይሌ አበበ ተናግረዋል።
ወቅታዊ የጸጥታ ኹኔታውን ተቋቁሞ ብዙ የማዕድን ነክ ተግባራት መሠራቱ እና በአመለካከት ደረጃ ሕዝቡ ለማዕድን ሃብት ያለው እሳቤ እየተሻሻለ መምጣቱ በጥንካሬ የሚነሳ እንደኾነ በሪፖርቱ ተካትቷል። ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው የጸጥታ ችግር፣ የማዕድን ላቦራቶሪ አለመኖር እና የአጋዥ ቴክኖሎጅዎች እጥረት መኖር ሃብቱን ባለው ልክ ለመጠቀም እንቅፋቶች እንደነበሩም ገልጸዋል።
በቀጣይ የክልሉን የማዕድን ልየታ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። ሲሚንቶ፣ ብረት እና የድንጋይ ከሰል ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። በጸጋው ልክ ማዕድን ለማምረት በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካል ርብርብ እንደሚያስፈልግም ቢሮ ኀላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን