የኅብረት ሥራ ማኅበራት ፍትሐዊ ግብይትን ለማስፈን እንደሚያስችሉ ተገለጸ።

39

አዲስ አበባ: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር እና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ከተማ ተከፍቷል። በሲንፖዚየሙ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

እንደ ሀገር ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር እና ሲንፖዚየም “የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተከፈተው። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልዕልቲ ግደይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በከተማዋ እና እንደ ሀገር የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሀገር ውስጥ የምርት እሴት ሰንሰለትን በማጠናከር፣ ፍትሐዊ ግብይትን በማስፈን፣ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል። የአደረጃጀት፣ የአሠራር እና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት የማኅበራቱን የዕድገት ጉዞ እየጎተተ መኾኑንም አንስተዋል።

ሲንፖዚየሙ ዜጎች ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እና አቅራቢዎች ምርት እና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል እንደኾነም ገልጸዋል። የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ እንደ ሀገር የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በግብርናው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። የኅብረት ሥራ ማኅበራት አምራቹን እና ሸማቹን በማገናኘት ረገድ ዛሬም ድረስ ያልተሻገሩት ችግር ነው ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ውጤታማ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል። በሲምፖዚየሙ የተሳተፉ የኅብረት ሥራ ማኅበር አባላት እና ዩኔየኖች ምርታቸውን በጥራት፣ በመጠን፣ በአይነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ከጥር 28/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በኤግዚቪሽን ማዕከል ይካሄዳል ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልዲያ ቆቦ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳይፈጠር ጊዜያዊ ተለዋጭ መተላለፊያ ተሠራ።
Next article“ኤች አይቪን በመከላከሉ ረገድ መዘናጋት አለ” አብዱልከሪም መንግሥቱ