
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) በደቡብ ክልል በቤት ለቤት ልየታ ሥራ ከ325 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተደራሽ ሆነዋል፡፡
በደቡብ ብሔሮ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በተካሄደው የቤት ለቤት ልየታ ሥራ ከ325 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ተደራሽ መደረጋቸውን የክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ገለጹ።
ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የኮሮና መከላከል ሥራ ወቅታዊ ሁኔታና ትኩረት በሚሹ የጤና ዘርፍ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ርስቱ ይርዳው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት የኮሮና በሽታን ለመከላከል የተጀመረው የቤት ለቤት ልየታ ሥራ ውጤታማ ሆኗል።
እስካሁን በክልሉ በ325 ሺህ ቤቶች የሚኖሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች በልየታው መታየታቸውንና አንድ የ45 ዓመት ሴት የኮሮና ቫይረስ ምልክት በማሳየታቸው በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል።
በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ጡጦ ሱጋሬ ነዋሪ የሆኑትና በአነስተኛ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ሴት ናቸው በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው፡፡ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንደሆነና ቫይረሱ በምን መልኩ ወደእርሳቸው እንደመጣ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሴትዮዋ መናገራቸውንም ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎ ከእርሳቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው 16 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ለክትትል እንደገቡ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ከኬንያ ሞምባሳ ወደ ሞያሌ ተመልሶ በዳዋ ማቆያ ምርመራ ያደረገ አንድ ሰው ውጤቱ ሳይገለጽ ወደ ሐዋሳ እንደተንቀሳቀሰ ገልፀዋል። ግለሰቡ በጉዞ ላይ እያለ ቫይረሱ እንደተገኘበት በምርመራ ውጤቱ በመታወቁ በክትትል ሀላባ ላይ ተይዞ ወደ ሕክምና ማዕከል እንዲገባ መደረጉም ታውቋል። ከግለሰቡ ጋር አብረው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ 41 ሰዎች መካከል 37ቱ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
4 ሰዎች እስካሁን ድረስ እንዳልተገኙና ፍለጋ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ርስቱ ከ37 ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሌሎች 113 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉንም መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ ቫይረሱ የተገኘባቸው የሁለቱ ሰዎች ጉዳይ የጤና ሚኒስቴር በተለያዩ ቀናት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።