በወልዲያ ቆቦ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳይፈጠር ጊዜያዊ ተለዋጭ መተላለፊያ ተሠራ።

44

ባሕር ዳር፡ ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወልዲያ ቆቦ መንገድ የሚገኘው የአሚድ ወንዝ ብረት ድልድይ መሰበሩን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳይፈጠር ጊዜያዊ ተለዋጭ መተላለፊያ መንገድ መሠራቱን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታውቋል። አሥተዳደሩ ድልድዩን በሌላ ለመተካት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

በአሥተዳደሩ የድልድዮችና ስትራክቸር ክፍል ዳይሬክተር ኢንጂነር ተክለስላሴ ንዳ እንደገለጹት፤ ትናንት ከሰዓት የአሚድ ወንዝ ብረት ድልድይ መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ የጫነ ተሽከርካሪ ሲሻገር የብረት ድልድዩ ተደርምሷል።

በዚህም በስፍራው የተፈጠረውን ትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል ለመፍታት አስተዳደሩ የግንባታ ማሽኖች ወደ ስፍራው ልኮ ተለዋጭ መንገድ በመሥራት ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም አነስተኛ ተሽከርካሪዎች በተለዋጭ መተላለፊያ መንገድ አገልግሎት እየሰጡ መሆን ገልጸዋል።

የብረት ድልድዩን በሌላ በመተካት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከወልዲያ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአሚድ ወንዝ ድልድይ 48 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዚን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
Next articleየኅብረት ሥራ ማኅበራት ፍትሐዊ ግብይትን ለማስፈን እንደሚያስችሉ ተገለጸ።