
አዲስ አበባ: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአዲስ አበባ ከተማ የአራት ኪሎ ፕላዛ የእግረኞች የውስጥ ለውስጥ ማሳለጫ መንገድ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በኮሪደር ልማቱ ሠርቶ ካጠናቀቃቸው በርካታ ሥራዎች መካከል አንደኛው የአራት ኪሎ ፕላዛ የውስጥ ለውስጥ የእግረኞች መሸጋገሪያ መንገድ ነው። የእግረኞች መሸጋገሪያ መንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያው ለአቅመ ደካሞች ዘመናዊ አሳንሰር ተገጥሞለታል። በውስጡ 17 ሱቆችን መያዙም ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ነፃነት ዳባ በዘመናዊ መንገድ የተሠራው እና ለተገልጋዮች ክፍት የኾነው የአራት ኪሎ ፕላዛ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከመሬት በታች የተሠራ የማሳለጫ መንገድ ነው ብለዋል።
መንገዱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደላውም ገልጸዋል። የተሳለጠ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የእግረኛ ፍሰት እንዲኖር እና የኅብረተሰቡ ደኅንነት እንዲጠበቅ ለማድረግም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የአራት ኪሎ ፕላዛ የውስጥ ለውስጥ የእግረኞች መተላለፊያ ማሳለጫ መንገድ የተሠሩ ሱቆች ለወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ናቸው ነው ያሉት።
ኀብረተሰቡም ከመሬት በታች የተሠራውን ዘመናዊ መሸጋገሪያ የራሱ ንብረት መኾኑን በመገንዘብ መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለበትም አሳሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!