የገበያ ማዕከላት ለጤናማ የገበያ ሥርዓት!

29

ባሕር ዳር: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረሰቡን የኑሮ ኹኔታ እየፈተነ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ ቋሚ የአምራች እና የሸማች መገናኛ የገበያ ማዕከል ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል። ቋሚ የአምራች እና የሸማች መገናኛ የገበያ ማዕከሎች ሕገ ወጥ ደላላን በማስቀረት በኩል ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሏል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክት ኀላፊ አትክልት አሳቤ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት በኩል ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል። በ2022 በሕግ እና በሥርዓት የሚመራ የንግድ እና የግብይት ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሮው አልሞ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከተያዙት የትኩረት ነጥቦች ውስጥ አምራቹን አካል ከሸማቹ በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከሎችን መገንባት ዋናው እንደኾነ ተናግረዋል።

ገበያውን በሥርዓት መምራት ከተቻለ የኑሮ ውድነቱን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት። በክልሉ ነባር የገበያ ማዕከሎች እንደተጠበቁ ኾነው በጀት ተይዞላቸው እየተገነቡ ያሉ 83 የገበያ ማዕከሎች በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ተግባሩ በክልሉ ባሉ ስምንት የሪጅዮፓሊታንት ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነው። የክልሉ መንግሥት ለጉዳዩ ተኩረት ሰጥቶ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል ነው ያሉት። ክልሉ ከበጀተው በጀት በተጨማሪ ከተሞቹም በራሳቸው ጭምር በጀት መድበው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል። ከስምንቱ የሪጅዮፓሊታንት ከተሞች ውስጥ አምስቱ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደ ገበያ ማዕከል ግንባታ ተግባሩ የገቡ ሲኾን ቀሪዎቹም በሂደት ላይ መኾናቸውን ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ገልጸዋል።

በሂደት ላይ ያሉት ወልድያ፣ ደብረ ታቦር እና ባሕር ዳር ከተማ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሁሉም ከተሞች የማዕከል ግንባታውን በአራት ወር መጨረስ እንዳለባቸውም አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት። ተግባሩ ከሪጅዮ ፓሊታንት ከተሞች በተጨማሪ ወደታች ባሉ ከተሞችም የሚሰፋ እንደኾነ ነው የገለጹት። ወደ ተግባር መገባቱንም ነው የተናገሩት።

በየከተማዎቹ ምቹ የገበያ ማዕከሎችን መገንባት ሸማቹን እና አምራቹን እንደ ድልድይ ኾነው የሚያገናኙ ይኾናሉም ብለዋል ምክትል ኀላፊዋ። የደላላን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ካላስፈላጊ የዋጋ ግሽበት የሚያድን ተግባር ነውም ብለዋል። “ጤናማ የገበያ ሥርዓትን ለመዘርጋት ዘመናዊ ቴክኖሎጅን የማበልጸግ ሥራ እየተሠራ ነው” ብለዋል ወይዘሮ አትክልት። ገበያውን ከሚያዛቡ ነገሮች ውስጥ አንዱ መረጃ ማዛባት በመኾኑ የዘመነ የግብይት መረጃ አያያዝን ለመከተል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይህ የገበያ ሥርዓቱ ለውጥ ያመጣ ዘንድም ማኅበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት አጋዥ እንዲኾኑ አሳስበዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኅላፊ ዮናስ እንዳለ ፈተና እየኾነ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ቋሚ የአምራች እና የሸማች መገናኛ የገበያ ማዕከሎች ትልቅ መፍትሄ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ጥቅሙን በመረዳትም በደሴ ከተማ 8 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ተለይቶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። በአራት ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀው ለመጨረስም አቅደው አየተንቀሳቀሱ እንደኾነ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። ማዕከሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የግብርና ምርቶች እና ሌሎችም መሠረታዊ ነገሮች የሚቀርቡበት ኾኖ እንዲገነባ እየተደረገ እንደኾነ ነው የተናገሩት።

የግንባታ ወጭውም በክልል እና በከተማ አሥተዳደሩ የሚሸፈን ነው ብለዋል። የማዕከሉ ዋና ዓላማ ጥራት ያለው ምርት ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ ማድረግ እና ገበያን ማረጋጋት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች መዳረሻ የገበያ ማዕከል ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በከተማው በተለምዶ አይራ በሚባለው አካባቢ 7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማዕከሉን ለመገንባት ሥራው ተጀምሯል ነው ያሉት። ለግንባታውም ክልሉ 58 ሚሊዮን ብር የፈቀደ ሲኾን ከተማ አሥተዳደሩ ደግሞ 102 ሚሊዮን ብር በድምሩ 160 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለት ወደ ተግባር እንደተገባ ነው የተናገሩት።

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ተስፋ ተጥሎበታል ነው ያሉት። ተግባሩን በሦስት ወራት ለማጠናቀቅ ታስቦ ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት እንደኾነም ገልጸዋል። ይህ ተግባር ሲጠናቀቅ ደላሎች መሐል ላይ የሚገቡበት አጋጣሚም የሚቀር ይኾናል ነው ያሉት።

የዘመናዊ የገበያ ማዕከሎቹ መገንባት ሸማቹ እና አቅራቢው በቀጥታ ይገናኙበታል፤ ሸማቹ ትኩስ ምርት በቀጥታ የሚያገኝበት ዕድል ይፈጥራል፤ ኑሮ ውድነትን በማርገብ ረገድም ድርሻው ትልቅ ይኾናል ነው የተባለው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ክልልን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ ሁለት የፍጥነት መንገዶች የግንባታ ጥናት እየተደረገ ነው።
Next article“የንግዱ ዘርፍ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ