
ባሕር ዳር፡ ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአዲስ አበባ በተለያዩ መስመሮች የሚወጡ 4 አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ጥናቱ እየተደረገ የሚገኘው ከአዲስ አበባ ደሴ፣ ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ ፣ከአዲስ አበባ ጅማ እና ከአዲስ አበባ ነቀምት በሚዘልቁት መንገዶች ላይ ነው፡፡
እነዚህ የፍጥነት መንገዶች የሚገነቡበት የጥራት ደረጃ ፣ የሚኖራቸውም አጠቃላይ የጎን ስፋት ከፍ ያለ እና የሚገነቡበት መልክአ ምድር አብዛኛውን ተራራማ ቦታዎችን የሚሸፍን በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ወጪ እና የቆረጣ ሥራዎችን የሚጠይቁ ናቸው፡፡
በጥናቱ መሰረት ፕሮጀክቶቹ የሚኖራቸው ርዝመት በአማካይ 300 ኪሜ ሲሆን ግንባታቸውም በተለያዩ ምዕራፎች እና በተወሰነ ኪሎሜትር ተከፋፍሎ የሚጀመር ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶቹ የአዋጭነት፥ እንዲሁም መሰረታዊ የዲዛይንና የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን ለዝግጅት ሥራው የሚያስፈልጉ የጥናት ሥራዎችንም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
አራቱን የፍጥነት መንገዶች ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው በመንግስትና የግል አጋርነት ትብብር ነው፡፡
ከፍጥነት መንገዶቹ መካከል የአዲስ ጅማ እና አዲስ ደብረ ማርቆስ ፕሮጀክቶች ለገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት የግል አጋርነት ቦርድ የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹም በቅርቡ ይቀርባሉ ተብለው ይጠበቃል ።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር መረጃ እንደሚያመለክተው ፕሮጀክቶቹም በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት የግል አጋርነት ትብብር ቦርድ ከጸደቁ በኋላ ወደ ቀጣይ ሥራ ይገባሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!