
ባሕር ዳር: ጥር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየወረዳው ባከናወናቸው የተሳታፊዎች ልየታ የሚያግዙትን ተባባሪ አካላት ለይቶ የመግባቢያ ስምምነት ሚያዚያ 12/ 2015 ዓ.ም መፈራረሙን አስታውሷል።
ኮሚሽኑ ይህንን የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋሟት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እና ከኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማኅበራት ጥምረት ጋር ነው።
እነዚህ አካላት ሲመርጡ የተለያዩ መስፈርቶችን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን ያስታወሰው ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት የሰጠው ግን የአካላቱ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን የመቋቋም ብቃት መኾኑን አንስቷል።
ኮሚሽኑ በሥራው ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ የጸጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመከላከል የወረዳ አስተዳዳሪዎችን እና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች የሂደቱ አካል እንዲሁኑ በአሠራር ሥርዓቱ ደንግጎ ውጤታማ የኾነ የተሳታፊዎች ልየታን ሲያከናውን ቆይቷል ነው ያለው።
ሆኖም ግን ኮሚሽኑ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና ዓውድ ላይ ተመሥርቶ ከላይ ከተጠቀሱት ተባባሪ አካላት በተጨማሪ ማኅበረሰቡ እምነት የሚጥልባቸውን ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት በተባባሪ አካልነት ማቀፉን አንስቷል።
በዚህ መሠረት፦
1. በአፋር ክልል
👉 የጎሳ መሪዎች
👉 የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች
👉የሼሪያ ፍርድ ቤት ዳኞች (ቃዲዎች)
👉 የሀገር ሽማግሌዎች (ሱልጣኔቶች)
2. በሶማሌ ክልል
👉የጎሳ መሪዎችን/የሀገር ሽማግሌዎችን/ ኡጋዞች
👉 የሸርያ ፍርድ ቤት ዳኞች
👉 ጀምአዎች (የሴቶች አደረጃጀቶች)
3. በኦሮሚያ ክልል
👉አባገዳዎች
👉 ሀደ ሲንቄዎች
👉የማኅበረሰብ መሪዎች፤
4. በአማራ ክልል
👉 የሀገር ሽማግሌዎች
👉 የሴቶች ማኅበራት
👉 የገበሬ ኅብረት ሥራ ማህበራት በተጨማሪነት ተመልምለው ኮሚሽኑን እገዛን እንዲያደርጉ ተደርጓል ብሏል።
ሁሉም ተባባሪ አካላት ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ሥልጠና በማዘጋጀት ተባባሪ አካላቱ በተሳታፊ ልየታ ሂደት እና አተገባበር በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል ነው ያለው።
ይህንንም ተከትሎ የተጨመሩት አካላት ወደሚገኙባቸው የተለያዩ ወረዳዎች በመሄድ በኮሚሽኑ ከተለዩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎችን በመለየት ሂደቱ ተዓማኒ እንዲኾን አመርቂ ሥራ ሠርተዋል ብሏል።
በእስከ ዛሬው ሂደት ኮሚሽኑ ከ6 ሺህ በላይ ለሚኾ ተባባሪ አካላት ሥልጠና በመስጠት የምክክር ሂደቱ በየማኅበረሰቡ ወግና እና እሴቶች ላይ የተመረኮዘ እንዲኾን ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።
ከኢትዮጵጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኮሚሽኑን ተዓማኒነትም ከፍ ለማድረግ ተችሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!