
ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የአማራ ክልልን ፍትሕ ቢሮ የሥራ አፈጻጸምም ገምግሟል። የቋሚ ኮሚቴ አባላት የፍትሕ ቢሮ ለዜጎች ፍትሕን ለማረጋገጥ እየሠራው ያለው ተግባር መልካም ነው ብለዋል። የሕግ ከለላ እና ድጋፍ በመስጠት በኩልም ጥሩ ሥራ እያከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
ነገር ግን አሁንም የሴቶችን እና ሕጻናትን መብት ከማስከበር አንጻር ጉድለቶች አሉ ነው ያሉት። ንብረታቸውን የሚዘረፉ፣ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። የፍትሕ ቢሮውም የዜጎችን መብት የማረጋገጥ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል። የፍትሕ ሥርዓቱ በሕዝብ ዘንድ ታዓማኒ እንዲኾን መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
የፍትሕ ቢሮው ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። የሰብዓዊ መብት አያያዝን ማስተካከል እንደሚገባም ነው የተናገሩት። በተለይም ከወቅታዊ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የሚታሰሩ ሰዎችን መብት በማስከበር በኩል ያለውን ክፍተት መሙላት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ በርሃኑ ጎሽም ተቋሙ የተጣለበትን ኀላፊነት ለመወጣት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻለ እንዲኾን በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል። ማድረግ የሚገባን እና ክፍተቶች እንዳሉብንም እንዳረለን ነው ያሉት። በክልሉ በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖችን መብት ለማስከበር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የሰበዓዊ መብት አያያዝን በተሟላ መልኩ ለማስከበር እንቅፋት መኾኑንም ጠቁመዋል። “በችግር ውስጥም ኾነው ለሰብዓዊ መብት መከበር በትኩረት መሥራታቸውን ነው” ያመላከቱት። የፖሊስ ጣቢያዎችን እና የማረሚያ ቤቶችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንደሚከታተሉ ነው የተናገሩት።
የፍትሕ ተቋማቱን በጅምላ መፈረጅ እና እንደማይገባ የተናገሩት ኀላፊው ለሙያቸው ታምነው የሚሠሩ ባለሙያዎችን እና መሪዎችን ማክበር ይጠበቃል ነው ያሉት። የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ባለሙያዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጭ የሚሠሩትን የምክር ቤት አባላት እና ማኅበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥም ጠይቀዋል። ከሕግ ውጭ በሚሠሩ እና ማስረጃ የተገኘባቸው ላይ እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውን እና ወደፊትም እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
ፍትሕ ቢሮው የሴቶች እና ሕጻናትን መብት ለማስከበር በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የሕግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንደሚሠራም ተናግረዋል። የፍትሕ፣ የፖሊስ፣ የማረሚያ ቤት ቅንጅት እየጠነከረ መኾኑንም አስረድተዋል።
ዜጎችን የፍትሕ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየተገበሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!