
ደባርቅ: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደባርቅ ከተማ አካሂዷል። በየደረጃው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ጤናማ የንግድ ሥርዓትን ለመገንባት ዘርፉን ማበረታታት እና ማዘመን እንደሚገባ ተደጋግሞ ይገለጻል።
ባለፉት ስድስት ወራት ገበያውን ለማረጋጋት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ በጀት በመያዝ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለጹት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ ናቸው።
ኀላፊው ባለፉት ወራት የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ከአጋር ተቋማት ጋር ሢሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ ሕገ-ወጥ ንግድን በግብረ-ኀይል የመከላከል እና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ካሉበት ቦታ የማቅረብ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል።
የጃናሞራ ወረዳ የንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ጌታቸው፣ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እና የተደረገውን የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን አንስተዋል። አማራጭ የምርት አቅርቦት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ውቤ ገብረማርያም የተራዘመ እና ያልተገባ የደላሎች ጣልቃ ገብነት የሚታይበትን የገበያ ሥርዓት፤ አምራቹን፣ ነጋዴውን እና ሸማቹን በማቀራረብ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመድረኩ፣ ጤናማ የንግድ ሥርዓትን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የአጋር ተቋማት ሚና ከፍተኛ በመኾኑ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ውጤታማ ተግባር ማከናዎን እንደሚገባም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!