
ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማቱን የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የጸጥታ ተቋሙ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እየከፈለው ያለው መስዋዕትነት ክብር የሚያሰጠው መኾኑን ገልጸዋል። በራስ አቅም የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራም የሚበረታታ ነው ብለዋል። በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት።
የሰላም እና የጸጥታ ተቋማት የሕዝብን መታገት፣ መገደል እና መጎዳት ማስተካከል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ለሕዝብ መስዋዕትነት የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ መረጃ የሚያወጡ ከመንግሥት በተቃራኒ የሚሠሩ የጸጥታ ኀይሎች አሉ ነው ያሉት። በአንድነት እና በቁርጠኝነት በመሥራት ሕዝብን ከችግር እና ከሰቆቃ ማውጣት ይገባል ብለዋል። ያለ ጥላና ከለላ የሚታገቱ እና የሚገደሉ ወገኖችን መታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸው ሀሳቦች እና አስተያየቶች ለቀጣይ ሥራዎች ወሳኝነት እንዳላቸው ነው የተናገሩት። የጸጥታ ኀይሉ በድል የደመቀባቸውን ውጤቶች አስመዝገቧል ብለዋል። ነገር ግን አሁንም መሙላት ያለብን ክፍተት አለብን ነው ያሉት።
የጸጥታ ኀይሉ በአንድነት፣ በቅንጅት፣ በታማኝነት እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በውስጥ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። ታጣቂ ኀይሉ አሁን ላይ የማድረግ አቅሙ ወርዷል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ ትልቅ ሥራ እየሠራ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው በተሠራው ሥራ የታጣቂ ኀይሉን አዳክሞታል ብለዋል።
አብዛኛው የጸጥታ ኀይል ታማኝ እና ለመለዮው የሚሞት መኾኑን ተናግረዋል። አንዳንድ ሌቦች እና እምነት የሚያጎድሉ መኖራቸውንም ገልጸዋል። እምነት የሚያጎድሉትን ደግሞ የማጥራት ሥራ መሥራታቸውን እና እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በጸጥታ ኀይሉ ውስጥ መረጃ የሚያሾልኩትን፣ ከታጣቂ ኀይሉ ጋር የሚሠሩትን እያጣራን ተገቢውን ማስተካከያ የማድረግ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። ታማኝነትን በማረጋገጥ ለሰላም በጽናት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሁላችንም ተጋግዘን መሥራት አለብን ነው ያሉት።
የጸጥታ ኀይሎችን መብት እና ጥቅማጥቅም ለማስከበር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኀይሉን ለማጠናከር እየሠራው ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የጸጥታ ችግሩ እንዲቋጭ እና ክልሉ ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ሰላም እና ድርድርን የማይቀበሉ ኀይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
አሁንም ችግሩ መፈታት ያለበት በሰላም ነው ብለዋል። ሰላም እና ድርድርን በመቀበል ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በሰላም የሚመጡትን እየተቀበልን፣ የማይቀበሉት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ዓላማው ክልሉን ከታጣቂ ኀይሉ ነጻ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም እንዲዞር ማድረግ ነው ብለዋል።
የጸጥታ ችግሩን በብስለት፣ በስክነት እና በውይይት መፍታት ይገባል ነው ያሉት። አሁን ካለበት የጸጥታ ችግር በአንድነት ጠንክረን መውጣት አለብን ያሉት ምክትል ኀላፊው የክልሉን የጸጥታ ችግር የምንፈታው ተባብረን ነው ብለዋል።
ግጭቱን በፍጥነት ወደ ሰላም በመቀየር ወደ ልማት መመለስ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ሕዝብን ከመንግሥት ጋር የሚያቀራርቡ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
የጸጥታ ኀይሉ ለሀገሩ፣ ለሕዝቡ እና ለመለዮው ታምኖ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል። ለዘላቂ ሰላምን ትብብርን እያጠናከሩ መቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!