የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ።

29

ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማቱን የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የጸጥታ ተቋሙ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እየከፈለው ያለው መስዋዕትነት ክብር የሚያሰጠው መኾኑን ገልጸዋል። በራስ አቅም የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራም የሚበረታታ ነው ብለዋል። መስዋዕትነት እየከፈለ በሠራው ሥራ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በጀግንነት እየታገለ ነው፣ ለዚህ ክብር ልንሰጠው ይገባል ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩን ሕግ በማስከበር ብቻ ሳይኾን በእርቅ እና በይቅርታ ለመፍታት እየተሄደ ያለው ርቀትም የሚበረታታ ነው ብለዋል። የጸጥታ ተቋሙ የክልሉን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመመለስ መስዋዕትነት ከመክፈል ባሻገር ውይይትን እንደ አማራጭ መጠቀም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ከሕዝብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል። የክልሉን ግጭት በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ በመቋጨት ሕዝቡን ከተራዘመ ጦርነት መውጣት ይጠበቃል ነው ያሉት። የሰላም እና የጸጥታ ተቋማት የሕዝብን መታገት፣ መገደል እና መጎዳት ማስተካከል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የጸጥታ ኀይሉን መፈተሽ እና ታማኝነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ለሕዝብ የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ መረጃ የሚያወጡ ከመንግሥት በተቃራኒ የሚሠሩ የጸጥታ ኀይሎች አሉ ነው ያሉት። በአንድነት እና በቁርጠኝነት በመሥራት ሕዝብን ከችግር እና ከሰቆቃ ማውጣት ይገባል ብለዋል። ከሁሉም አስቀድሞ ስለ ሰላም መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብን እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት መመለስ ይጠበቃል ነው ያሉት። መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙ ሚሊሻዎችን ማበረታታት እና ለላቀ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። የአካባቢውን ሰላም በቁርጠኝነት የሚጠብቅ ማኅበረሰብ አለ ያሉት አባላቱ የማኅበረሰቡን ተሞክሮ ማስፋት እና በጋራ ሰላምን ማጽናት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ለሀገር እና ሕዝብ የሚጠቅሙ ባለሙያዎችን እና መሪዎችን መጠበቅ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል ግርማ ገሠሠ የክልሉ የጸጥታ ኀይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ስምሪት ሲወስድ መቆየቱን ተናግረዋል። አሁን ደግሞ ራሱን እየቻለ በወረዳዎች ላይ ሰላምን እያስከበረ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ እየሰፋ ሲሄድ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ ይሄዳል ነው ያሉት። አሁን ላይ እየተወሰደ ባለው ርምጃ ታጣቂው ኀይል እየተዳከመ፣ እየተበተነ እና አቅም እያጣ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሚያግቱ፣ የሚሰርቁ እና የሚገድሉ ወንጀለኞችን ማኅበረሰቡ ሊታገላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪው ኀይል ለክልሉ ሰላም ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መኾኑን ገልጸዋል።

የጸጥታ ኀይሎችን ማበረታታት እና ጥቅማቸውን ማስከበር እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። በክልሉ ያለው ጦርነት ግንባር የሌለው እና የእርስ በእርስ በመኾኑ ውሥብሥብ እንዳደረገውም አንስተዋል። የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትልቅ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ነገር ግን የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተካከለ መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኪሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ የተፈጠረው የፖለቲካ ብልሽት የጸጥታ ኀይሉ ሥራ ላይ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት። አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን መረዳት ይጠበቃል ብለዋል። ነገር ግን አሁንም የሚፈጸሙ ወንጀሎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

ለክልሉ ሰላም በቁርጠኝነት የሚሠራ የጸጥታ ኀይል መኖሩንም አንስተዋል። በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎችን ወደ ዞን ፍርድ ቤቶች እየወሰዱ ጉዳያቸው እንዲታይ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሕዝብ የሰላም ዋስትና እንዲኖረው በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅ ያነሱት ኮሚሽነሩ ችግሮችን ለመፍታት የጸጥታ ኀይሉ እየሠራ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊሲ ኮሚሽን ኮሚሽን ደስዬ ደጀን የጸጥታ ኀይሉ የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል። የክልሉ የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ አሁን ሥራ የሚያስፈልጋቸው እና በፍጥነት መሻገር የሚያስፈልጉ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት። የውስጥ አንድነትን ማስተካከል እና የውስጥ ችግሮችን መፍታት ይጠበቃል ብለዋል።

የክልሉን የጸጥታ ችግር ለማሻሻል የጸጥታ ኀይሉ ኀላፊነት ብቻ አለመኾኑንም አመላክተዋል። በክልሉ የግድያ፣ የዘረፋ እና የእገታ ወንጀሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ዘረፋን እና እገታን የሀብት ምንጭ አድርገው የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል። ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ማኅበረሰቡም ተባባሪ እንዲኾን አሳስበዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ትልቅ ሥራ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝቡም ለጸጥታ ኀይሉ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ፖሊስ በግጭት ውስጥ ኾኖም በርካታ መደበኛ ሥራዎች ሠርቷል ነው ያሉት። የጸጥታ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ክልሉ ወደ ኋላ ቀረ? ለምን ሰላማችን አጣን? የሚለውን ሁሉም እየጠየቀ ከሠራ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል “ግብርና ቢሮ
Next articleአሁንም ችግሩ መፈታት ያለበት በሰላም ነው።