“8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል “ግብርና ቢሮ

53

ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚከታተላቸውን የግብርና፣ የውኃ እና ኢነርጂ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ፣ የመሬት ቢሮ እና የደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ እየገመገመ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው ለ2017/18 የምርት ዘመን አዳዲስ እሳቤዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። በክልሉ ሜካናይዜሽንን ማስፋት ቢታሰብም ውስንነት አጋጥሟል ያሉት አቶ ቃልኪዳን ቢሮው ችግሩ እንዲፈታም መዋቅር ተሠርቷል ብለዋል።

ከፍተኛ ፍላጎት እና መነሳሳትንም ፈጥሯል ነው ያሉት። አርሶ አደሩም ለዚሁ ተግባር የሚውል ብር እየቆጠበ መኾኑንም ገልጸዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ “8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ እንደኾነ” ገልጸዋል። የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ስምንት መርከቦችም ጅቡቲ ወደብ ደርሰዋል ነው ያሉት።

ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ የማደበሪያ አቅርቦት አለ ያሉት ወይዘሮ ሙሽራ የተገዛውን ማዳበሪያ ለማሰራጨት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። ዳይሬክተሯ መንግሥት ማዳበሪያን በድጎማ እንደሚያመጣ ነው የገለጹት። አርሶ አደሮች በብድር የወሰዱትን የማዳበሪያ ገንዘብ መመለስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በ2016/17 የምርት ዘመን 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር አለመመለሱን ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የእንስሳት በሽታን ተጽዕኖ በመረዳት ችግሩን በጋራ ትብብር ልንሻገረው ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ።