ባለፉት ስድስት ወራት 27 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

25

እንጅባራ: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እና የቀጣይ ተግባራት ንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ከተሞችን ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የሚያስችሉ 77 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ለዚህም ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት 27 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ነው ያሉት። የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ጥራታቸው የተጠበቀ እና የከተሞችን ዘላቂ ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው አንስተዋል።

የከተሞችን ዘላቂ ዕድገት የሚገቱ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች ላይ በተወሰደው ርምጃ ባለፉት ስድስት ወራት 415 ሕገ-ወጥ ግንባታዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት ።

የተቋሙን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለማዘመን በተፈጠረው ተነሳሽነት አዘና እና ቻግኒ ከተሞችን ጨምሮ በስድስት ከተሞች የዲጂታል ሥርዓት ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተተገበሩ እንደኾነም ተናግረዋል።

የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ለ150 ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ለማስተላለፍ የሚያስችል የካሳ ስሌት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም በመድረኩ ተነስቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች ተስፋ የሚሰጡ መኾናቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
Next article“የእንስሳት በሽታን ተጽዕኖ በመረዳት ችግሩን በጋራ ትብብር ልንሻገረው ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ