የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች ተስፋ የሚሰጡ መኾናቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።

54

ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

በግምገማው ፍርድ ቤት ላይ እየተሠራው ያለው የለውጥ ሥራ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። እየተደረገ ያለው የለውጥ ሥራ የሚያነቃቃ እና ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል። የዳኝነት ሥርዓቱ የሚሻሻልበት እና ማኅበረሰቡ መልካም የዳኝነት ሥርዓት ያገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው ብለዋል። አሁን ያለው ተስፋ እውን እንዲኾን መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

በአጭር ጊዜ እያመጣው ያለው ለውጥ ለሌሎች ተቋማትም በተሞክሮነት የሚቀርብ ነው ብለዋል። የለውጥ ሥራው የበለጠ መሬት እንዲነካ እና መሠረት እንዲይዝ ማድረግ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። የተቋም ግንባታ ጅማሮው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት። ነጻና እና ገለልተኛ ተቋም ለመገንባት የሚያስችል ተስፋ እንዳሳየም ገልጸዋል።

ሠራተኞች በአዲስ የሥራ መንፈስ ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገበት መንገድም የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል። ተስፋ ከሚሰጡ ሥራዎች በተቃራኒ በፍርድ ቤቶች ላይ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን መፍታት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። ከጸጥታ ችግሩ ጋር ተያይዞ በታችኛው መዋቅር በርካታ ችግሮች አሉ እነርሱን ማረም እና ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።

የፍትሕ ማሻሻያ ሥርዓቱንም በጥንቃቄ እንዲታይ አንስተዋል። የዳኞች እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉም ገልጸዋል። በዳኛ እጥረት ዜጎች ተገቢውን ፍርድ እያገኙ አይደለም ብለዋል። የዳኞችን የሥነ ምግባር ችግር ማስተካከል እንደሚጠበቅም አንስተዋል። የፍርድ ቤቱ የለውጥ ሥራ በአንድ ሰው ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይኾንም አሳስበዋል። ሁሉም የለውጡ አካል እንዲኾኑ እና ለውጡ ቀጣይነት ያለው እንዲኾን አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ዳኛ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነጻ ኾኖ መሥራት አለበት ብለዋል። ፍርድ ቤቱ ዳኞች በነጻነት እንዲሠሩ ይፈልጋል፣ ችግር ባለባቸው ላይ ደግሞ እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት። ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኞች መኾናቸውንም አመላክተዋል።

አሁን የተጀመሩ ለውጦች ለዳኞች ተስፋ የሰጡ መኾኑንም ገልጸዋል። ዓላማችን በክልሉ ነጻ እና ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር ማድረገ ነው ብለዋል። ይህ እንዲኾን ደግሞ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ፍርድ ቤቶች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ማክበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ መኾኑን ተናግረዋል። የዳኞችን ውሳኔ ያለ ማክበር ችግሮች እንዳሉም አንስተዋል። ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ የሚደርስባቸው እንግልት ሊቀር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወደ ታች እየወረደ እየደገፈ መኾኑን ገልጸዋል። ምክር ቤቱም ኾነ የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት የፍርድ ቤት ነጻነትን መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በፍርድ ቤት እየተሠሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በፍርድ ቤቶች የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የዳኝነት እጥረቱን ለመፍታት እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ጥራት ያላቸው ዳኞችን ለማፍራት እና የዳኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ልምድ ያላቸውን ዳኞች በተቋሙ ለማቆየት እንሠራለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የፍርድ ቤት ነጻነት እንደተጠበቀ ኾኖ የፍርድ ቤት ሥራዎችን ከሚደግፉ አካላት ጋር እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የተጀመረውን ለውጥ የሚሸከም የሰው ኃይል እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። የለውጥ ሥራዎች በአሠራር እና በሕግ እንዲደገፍ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስለአራጣ የወንጀል ሕጉ ምን ይላል?
Next articleባለፉት ስድስት ወራት 27 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።