
ባሕር ዳር: ጥር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አራጣ ያለው ለሌለው በተጋነነ የወለድ መጠን ወይም የተጋነነ ትርፍ ለማግኘት በገንዘብም ኾነ በቁስ መልኩ ማበደርን የሚመለከት የተከለከለ ተግባር ነው። ሰዎች ማጣታቸውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ራስን ብቻ በማስቀደም ትርፍን ለማጋበስ መሞከር በመኾኑ እንደሚያስቀጣ በወንጀል ሕጉ በግልጽ ተቀምጧል።
በ1996 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 712 ላይም የተቀመጠው ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። አለምነህ ሹመቴ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል አቃቢ ሕግ ባለሙያ ናቸው። የአራጣ ወንጀል ከግለሰብ ተጽዕኖው በዘለለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ እንደኾነ ይገልጻሉ።
ሰዎች የአበዳሪ እና የተበዳሪ ጣጣ ውስጥ በመግባት፣ የበላይ እና የበታች አስተሳሰብ እንዲነግስ በማድረግ ማኅበራዊ ግንኙነቱ እንዲላላ ያደርጋል ብለዋል። ሰዎች በገንዘብ ምክንያት አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግም ነው።
ከኢኮኖሚ አንጻርም ቢኾን ችግራቸውን ለመድፈን ብለው ከሚገቡበት ጣጣ መመለስ ሲያቅታቸው በገቡበት ውል መሠረት ሙሉ ንብረታቸውን ሸጠው በመክፈል ለግለሰባዊ ድህነት እና ጉስቁልና የሚዳረጉበት ዕድል መኖሩን የአቃቢ ሕግ ባለሙያው አለምነህ ሹመቴ ተናግረዋል።
ለዚህ የሚዳርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች የኢኮኖሚ አቅም ማነስ፣ የአበዳሪ ተቋማት ሥርዓት አለመመቸት እና የማኅበረሰቡ የግንዛቤ አድማስ አለመዳበር ተጠቃሾች ናቸው። ይሁን እና በሀገሪቱ የወንጀል ሕግ መሠረት የአራጣ ብድርን በሚከውኑ ግለሰቦች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ቅጣት ድረስ እንደሚያስጠይቅም ገልጸዋል።
በአዲሱ የወንጀል ሕግ መሠረት ማንም ሰው የግለሰቡን አቅም ማጣት፣ ብሶቱን አይቶ እና ከሕግ በወጣ መንገድ የተጋነነ ወለድ በማሰብ፤ ውል በማስያዝ ያበደረ እንደኾነ የጉዳዩ ክብደት እና ቅለት ታይቶ ከአምስት እስከ 10 ዓመት ጽኑ አስራት ሊያስቀጣ ይችላል ብለዋል።
የተጠያቂነት ልኩ እንደሠሩት የወንጀል አይነት ይለያይ እንጅ አበዳሪ ግለሰቡ ብቻ ሳይኾን ለወንጀሉ መተግበር ተባባሪ በመኾኑ ተበዳረውም በሕግ የሚጠየቅበት አግባብ ይኖራል።
ሕግ የሚሰርጸው እና ተግባራዊ የሚኾነው በግንዛቤ ደረጃ ከማኅበረሰቡ በጎ አመለካከት ካለ ነው። ይህም ያለ አግባብ መበልጸግ የሚያስቡትን የሚታገል እና ሕግ እንዲከበር የራሱን ጠጠር የሚወረውር ካለ ነው።
ሰዎች ከሕግ ባፈነገጠ አኳኋን ብድር የሚሰጡም ኾነ የሚቀበሉ ከኾነ ወንጀልነቱን የሚያሳይ መረጃ ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ የፍትሕ ዓይን እና ጀሮ መኾን ሲችል ነው። በሌላ በኩል የብድር አማራጮች የሚመቻቹባቸውን ስልቶት ማቅረብ ከመንግሥት የሚጠበቅ ሌላው ነጥብ እንደኾነም የአቃቢ ሕግ ባለሙያው አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!