
“በቀውስ ወቅት ትክክለኛ፣ ያልተዛባ፣ ወቅታዊ እና ተደጋጋሚ መረጃ ለሕዝብ ማድረስ ‹የማኅበረሰብ ክትባት› ተደርጎ ይወሰዳል፡፡” ዶክተር አደም ጫኔ-የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር
በቀውስ ወቅት የተግባቦት ሥልት ምን መሆን አለበት?
ወቅቱ ዓለማችን በሁሉም አቅጣጫ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀውስ ውስጥ የገባችበት ነው፡፡ ከሃያላኑ እስከ ህዳጣኑ የኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየፈተናቸው ይገኛሉ፡፡ ከሩቅ ምስራቃዊቷ ሃገረ ቻይና በወርሃ ታህሳስ እንደተነሳ ስለተነገረለት የኮሮና ቫይረስ ማንም ዓለምን በዚህ ፍጥነት እና ሁኔታ ይፈታተናታል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ ዳሩ የነበረው እንዳልነበረ እስኪመስል ድረስ ቅንጡ ከተሞች ተዘጋግተው፣ የአምልኮ ስፍራዎች ጭር ብለው፣ ሉላዊነትን የሻተችው ዓለም ከግራ ቀኝ ድንበሮቿ ተዘጋግተው፣ ሚሊየኖች በሆስፒታል ይገኛሉ፤ እልፎች ደግሞ ይህችን ዓለም እስከወዲያኛው ተሰናብተዋል፡፡ በበርካታ ሃገራት የቫይረሱ ስርጭት በተዘናጉበት ወቅት የተከሰተ መሆኑ ደግሞ ለቁጥጥር ቀርቶ በወጉ ለመቅበር እንኳን እስካለመቻል እንደተደረሰ ላስተዋለ ወቅቱ “የዓለማችን የቀውስ ወቅት” እንደሆነ ይገነዘባል፡፡
በኢትዮጵያም ወረርሽኙን በተመለከተ በተለይም የብዙኃን መገናኛ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ብቻ ሁሉም በሚችሉት ሁሉ ሳይታክቱ ለሕዝብ መረጃ ያደርሳሉ፡፡ የሚደርሰው መረጃ የመብዛቱን ያክል ግን ተፈላጊውን የባህሪ ለውጥ አላመጣም፣ የመረጃዎች መብዛትም የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ የሚሉ አስተያየቶችን እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ የቀውስ ወቅት ተግባቦት የስነ ልቦና ጫና ይኖረው ይሆን? ስንል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አደም ጫኔን አነጋግረናቸዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ለዚህ ዓለማቀፋዊ የጤና ቀውስ መገናኛ ብዙኃን፣ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ በበጎ ጎኑ ያዩት ዶክተር አደም መረጃ በቀውስ ወቅት ሃብት ብቻ ሳይሆን እስትንፋስም ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ “መልዕክትን ደጋግሞ ማሰማት አንዱ የተግባቦት ጥበብ ነው፤ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ተደራሽ ያልሆኑ ግለሰቦች መረጃውን እንዲያገኙ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር መልዕክት ሲደጋገም ለስርፀት እና ለመረዳት እድል ይሰጣል” ብለዋል ዶክተር አደም፡፡
“በቀውስ ወቅት ትክክለኛ፣ ያልተዛባ፣ ወቅታዊ እና ተደጋጋሚ መረጃ ለሕዝብ ማድረስ ‘የማህበረሰብ ክትባት’ ተደርጎ እንደሚወሰድ ጥናቶች ያመላክታሉ” ያሉት ምሁሩ ከዚህ በተቃራኒ የተጋነነ፣ የተዛባ፣ ሐሰተኛ እና ወቅታዊ ያልሆኑ መረጃዎች ሲሰራጩ የስነ ልቦና አደጋ እንደሚኖራቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ያለንበት የጤና ቀውስ ወቅት የተግባቦት ሂደቱን ለማጥናት እድል የማይሰጥ በመሆኑ እየቀያየሩ፣ ለውጡን እያስተዋሉ እና ተደራሽ ያልሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ግምት ውስጥ እያስገቡ የስርፀቱን ሂደት ማስቀጠል እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው