
ፍኖተ ሰላም: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሚሊሻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ለተከታታይ ቀናት ሲያሰለጥናቸው የነበሩ የ2ኛ ዙር የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላትን በፍኖተ ሰላም ከተማ አስመርቋል
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በመከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ማዕከል ኀላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ተመራቂ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላት ማኅበረሰቡ የተጋረጠበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋጋት ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የአካባቢውን ሰላም በራስ አቅም ለመቆጣጠር እና ችግሮችን በራስ ለመፍታት የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ብሎም የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ያስገነዘቡት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሙሉጌታ ዓለም ሰላም የሚረጋገጠው በፍላጎት ብቻ ሳይኾን ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን የሰላም አስፈላጊነትን ማስገንዘብ ሲቻል ብቻ እንደኾነ ነው ያብራሩት።
መምሪያ ኀላፊው ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማረጋጋት በሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላትን በማሠልጠን የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
ተመራቂ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላት የጸጥታ ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ ኅብረተሰቡ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መጋለጡ ወደ ሰላም አስከባሪ እና ሚሊሻ አባልነት ለመግባት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እና አካባቢያቸውን ወደ ነበረ ሰላሙ ለመመለስ ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተመራቂ አባላት አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!