
ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት “ከቃል እስከ ባሕል›› በሚል መሪ መልዕክት ከጥር 23/2017 ዓ.ም እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛው መደበኛ ጉባኤ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ ጉባኤው በድምቀት እና ዓላማውን ባሳካ መልኩ ስለመጠናቀቁ ገልጸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ለፓርቲውም ኾነ ለሀገሪቱ በሚመጥን ከፍ ያለ ደረጃ የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የተሳካ እንዲኾን አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ይህ ጉባኤ በአንደኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም በጥልቀት የተገመገሙበት፣ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የተሻሻለበት፣ በአሠራር መሠረት ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ አግባብ የአመራር አካላት የተመረጡበት ነበር ብለዋል፡፡
ጉባኤው የእስከአሁኑን ስኬቶች እና ድሎችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሱ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደነበርም ነው ያስገነዘቡት።
በጉባኤው የተቀመጡትን አቅጣጫዎች በውጤታማነት በመፈፀም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞ ለማፋጠን ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!