
ደብረ ማርቆስ፡ ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እና የጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት በትብብር ለመሥራት ውይይት አካሂደዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እና የጎዛምን ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኞች የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ቅንጅት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል በትብብር መሥራት አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷልም ብለዋል። የፍትሕ ተቋማት ተቀናጅተው ሲሠሩ ፍትሕን ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር አስተዋጽኦው የጎላ መኾኑ ተነስቷል። በፍትሕ ተቋማት ያለውን የሥራ ግንኙነትም ለማጠናከር ኾነ የሠራተኛውን የሥራ ስሜት ለማሳደግ እና የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ባዬ ጌታቸው በትብብር እና በቅንጅት መሥራት የፍትሕ ተቋማት በሕዝብ ዘንድ አመኔታ እንዲኖራቸው፣ የጋራ ችግሮችን በጥናት በመለየት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሙያዊ እና ተቋማዊ ነጻነትን ባከበረ መንገድ የሚሠራበትን ዕድል የሚፈጥር ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመሥገን ዜጎች በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት መፍጠር ከቻሉ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል። ትክክለኛ የዳኝነት ሥርዓት ሲኖር በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ጠንካራ መተማመን ይፈጥራል፤ ይህ እንዲኾን ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የፍትሕ እና የዳኝነት አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እና የጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር ለፍትሕ ሥርዓቱ እና ለዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በቅንጅት መሥራታቸው ሕዝብን የሚያሳትፍ፣ ተደራሽነትንም የሚያረጋግጥ ሊኾን እንደሚገባሞ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
ፍትሕ ለሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመኾኑ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!