
ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። ምክር ቤቱ የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ እና የተጠሪ የተቋማትን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የጸጥታ መዋቅሩ በክልሉ ሕግን ለማስከበር ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ በከፈለው መስዋዕትነት የክልሉን ሰላም በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል መቻሉንም ተናግረዋል።
የጸጥታ መሪዎቻችን ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ጽፈዋል ነው ያሉት። የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ትግል ውስጥ በጀግንነት በመታገል ለሕዝብ ሰላም ሠርተዋል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ በክልሉ የነበረውን አስቸጋሪ የጸጥታ ችግር እና አካሄድን ቀልብሷል ብለዋል።
የታጣቂ ቡድኑን አቅም የማሳጣት እና ከጥቅም ውጭ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የአካባቢውን ሰላም በራሱ አቅም የመምራት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ኹኔታውን የመቀልበስ፣ የማረጋጋት ፣ የማጽናት፣ እግር የመትከል እና የምሉዕነት ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል።
የታጣቂ ቡድኑን የመረጃ ምንጭ ማድረቅ እና እርምጃ የመውሰድ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ክልሉ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። የክልሉን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ ከተሠሩ መልካም ሥራዎች ጎን ለጎን ችግሮች እንደነበሩም ገልጸዋል።
ለሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ የማወያየት ክፍተቶች እንደነበሩም ተናግረዋል። በራስ አቅም የአካባቢውን ጸጥታ ከማስጠበቅ ይልቅ ሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲመጡለት የመፈለግ አዝማሚያ ያለባቸው አካባቢዎችም አሉ ብለዋል።
የታጣቂ ኃይሉ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እንደ ሽፋን በመውሰድ የአማራን ሕዝብ አጎሳቁሏል ነው ያሉት። ለአማራ ሕዝብ እቆረቆራለሁ እያለ ከአማራ ሕዝብ ጠላቶች ጋር እየሠራ ነው ብለዋል። አማራን ከጠላቶቹ ጋር ኾኖ የሚወጋ ኀይል መኾኑንም ገልጸዋል።
ታጣቂ ኀይሉ የማድረግ አቅሙ መድከሙን እና መዋጋት ከማይችልበት አቅም ላይ መድረሱንም ተናግረዋል። ታጣቂ ኀይሉ የክልሉ ሕዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይገባ እና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመራ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
መንታ መንገድ ላይ የቆሙ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ይህ አካሄድ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እንቅፋት እንደሚኾን ነው ያመላከቱት።
በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾነው በርካታ የጸጥታ ኀይል ማሰባሰባቸውን እና ሥልጠና መሥጠታቸውንም ተናግረዋል። የሠለጠነው የጸጥታ ኀይል ታሪክ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የጸጥታ ኀይሉን የማጠናከር እና ኀይሉን እየጨመሩ የመሄድ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ እየወሰዳቸው ያሉ ሥልጠናዎችን ሕዝቡ የደገፋቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ሕዝቡ ጠንካራ የጸጥታ ኀይል እንዲኖር ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት። የጸጥታ ኀይሉን ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት መስዋዕትነት እየከፈለ መኾኑንም ተናግረዋል። የክልሉን ሰላም ለማስከበር የተሠራው ሥራ መልካም መኾኑን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ከዚህ በላይ በመሥራት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ ብቻ በርካታ የታጠቁ ኀይሎች ለሰላም እጅ መስጠታቸውንም ተናግረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የታጣቁ ኀይሎችም ከጥቅም ውጭ እንዲኾኑ ተደርገዋል ነው ያሉት።
በክልሉ ከከፍተኛ የማኅበረሰብ ቁጥር ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። የጸጥታ ኀይሉን በትጥቅ እና በስንቅ የተሟላ እንዲኾን መሠራቱንም ገልጸዋል።
ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሰላም ዙሪያ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። ኅብረተሰብን ማዕከል ያደረገ የወንጀል መከላከል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
የጸጥታ ኀይሉ ወቅታዊውን የጸጥታ ችግር ከማረጋጋት ባለፈ መደበኛ ሥራዎችንም እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!