ተፈናቃዮችን መደገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።

27

ደሴ: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አግማስ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ባገኘው ድጋፍ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሀርቡ መጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ወገኖች የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል። ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች አሁን ያሉበት ኹኔታ አስቸጋሪ መኾኑን ገልጸው ሌሎች ወገኖችም ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አግማስ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተከታታይ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን የፕሮግራሙ አሥተባባሪ ኢሳ መሐመድ ተናግረዋል። አሥተባባሪው ዛሬ በመጠለያ ካምፑ ለሚገኙ ወገኖች የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል። አቶ ኢሳ ለድጋፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አመሥግነው በተለያዩ ችግሮች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች ድርጅታቸው የሚሰጠው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

አግማስ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ያደረገው የአልባሳት ድጋፍ የሚበረታታ እና ሌሎችም ሊጋሩት የሚገባ እንደኾነ በደቡብ ወሎ ዞን ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የአደጋ መከላከል እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አሥተባባሪ መሐመድ ሰይድ ተናግረዋል።

አሥተባባሪው በደቡብ ወሎ ዞን ከ41ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች እንዳሉ በማስታወስ ብዙዎቹ ወገኖች ግን አስቸኳይ እርዳታ እንደሚሹ እና ለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ይስሃቅ ኃይሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል።

የተደረገው የአልባሳት ድጋፍም በካምፑ ለሚገኙ ወገኖች ችግሮችን የሚያቃልል መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት ዝርዝር
Next articleባለፉት ስድስት ወራት ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከንክኪ ነጻ መደረጉን የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።