“በቀውስ ወቅት ተግባቦት የሚሠራጭ መረጃ ዓላማው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት ወይም መዘናጋት እንዳይፈጠር ማድረግ ነው፡፡” አደም ጫኔ (ዶክተር)

576

“በብዙኃን መገናኛዎች መልእክት ተላለፈ ማለት ታዳሚው ተረድቶታል ለማለት ዋስትና አይሆንም፤ የሥነ ልቦና ምላሾችን ማጤን ያስፈልጋል፡፡” ግዛቸው አስናቀ (ዶክተር)

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደገባ ከተነገረበት መጋቢት መጀመሪያ ሳምንት አንስቶ ነገሮች በብዙ መንገድ ተቀይረዋል፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራ ተቋርጧል፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ከመደበኛው ሥርዓት በተለየ ሁኔታ ሕግ የማስከበር ሥራ ይከወናል፤ ቱሪዝሙ ቆሟል፤ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴው ተዳክሟል፤ ፖለቲካችን ተቀዛቅዟል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ስብከት፣ የፖለቲከኞች ስሜት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ጭንቀት፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ትርዒት እና የብዙኃን መገናኛዎች ጩኸት ኮሮናን በሚመለከት ብቻ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ነገር ግን ከተሠራው ሥራ አንፃር የመጣው የባሕሪ ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ችግሩ ምንድን ነው? ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡

ለዘመናት ሲንከባለል የመጣው የፖለቲካል-ኢኮኖሚው እዳ በወቅቱ የጤና ቀውስ ተግባቦት ላይ ተጽእኖ ማሳረፉን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አደም ጫኔ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡ ውጤታማ የሚሆን የቀውስ ወቅት ተግባቦት መተማመንን መገንባት አለበትም ብለዋል፡፡ ‘‘በጤና ቀውስ ወቅት የማኅበረሰቡ አቀባበል እና የሳይንስ ምክረ ሐሳብ ሊለያዩ ይችላሉ’’ ያሉት ዶክተር አደም በቀውስ ወቅት ተግባቦት የሚሠራጭ መረጃ ዓላማው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት ወይም መዘናጋት እንዳይፈጠር ለማድረግ በመሆኑ መከተል ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶክተር አደም ዕይታ ለተፈጠረው መዘናጋት አደጋውን ሩቅ አድርጎ መመልከት፣ የተሟላ መረጃ አለመኖር፣ እስካሁን ምንም አልሆንም ብሎ መዘናጋት እና በመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ አናሳ መሆን ችግሮቹ ናቸው፡፡

በኮሮና ቫይረስ ስርጭት የቀውስ ወቅት ተግባቦት በብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ተከታታይነት ያለው ሽፋን መሰጠቱ መልካም እንደሆነ የገለጹት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና መምህር እና ሐኪም ዶክተር ግዛቸው አስናቀ ናቸው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የቀውስ ወቅት ተግባቦት ሐኪሞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ሰዎች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚሉት በርካታ ጠቃሚ ነገር ይኖራል የሚሉት ዶክተር ግዛቸው የመልእክት መደበላለቅ እንደሚስተዋልም ተናግረዋል፡፡

‘‘በብዙኃን መገናኛዎች መልእክት ተላለፈ ማለት ታዳሚው ተረድቶታል ለማለት ዋስትና አይሆንም፤ የስነ ልቦና ምላሾችን ማጤን ያስፈልጋል’’ ብለዋል ዶክተር ግዛቸው፡፡ ጭንቀትና ፍርሃት፣ ግራ መጋባት እና ሁኔታዎችን መካድ የሚስተዋሉ የሥነ ልቦና ምላሾች በመሆናቸው ሕዝቡ የመረጃ ምንጮቹን እንዲለይ፣ በቀን በተወሰነ ጊዜ ብቻ ዘገባዎችን መከታተል እንዳለበት እና እረፍት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክር ሰጥተዋል፡፡

‘‘ከብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ብቻ ወደ ሕዝቡ የሚፈስሰው የመረጃ ስርጭት የኅብረተሰብን ተሳታፊ አያደርግም’’ ያሉት ዶክተር አደም ናቸው፡፡ ቀልጣፋ ውጤታማ እና ተደራሽ የሆነ ተግባቦት ለመከወን ዘመናዊውን ብቻ ሳይሆን ባህላዊ የሆኑ የሕዝቡን አደረጃጀቶች መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ተግባቦት እየፈተሹ መጠቀም፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ማሳተፍ እና እስከ ታች ድረስ ያሉ የሃይማኖት አባቶችን በጉዳዩ ተሳታፊ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

በተለይም የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የሚጠቀሟቸውን ቃላት ሊመረምሩ እና ሊያሻሽሉ ይገባል ያሉት ምሁራኑ ‘‘በዚህ የጤና ቀውስ ወቅት እየተጠምናቸው ያሉት አንዳንድ ቃላት የትርጉም አሻሚነት፣ እርባና ቢስ እና ለሥነ ልቦና ጫና የሚዳርጉ ናቸው’’ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleከጥራት ደረጃ በታች የሆኑ ከ2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ታገዱ፡፡
Next articleበቀውስ ወቅት የተግባቦት ሥልት ምን መሆን አለበት?