ከ47 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ማስመለሱን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ገለጸ።

52

ባሕር ዳር: ጥር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የቢሮውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም የፍትሕ ቢሮ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አቅዶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በውስጡ በርካታ አምዶች እንዳሉት ተናግረዋል። የመሠረተ ማኅበረሰብ የፍትሕ ሰጭ አካላትን ማጠናከር አንደኛው አምድ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ኀላፊነትን የመፈተሽ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።

የፍትሕ ዘርፍ መሪዎችን እና ባለሙያዎችን ለማጥራት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ያደገ እና ውጤታማ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን አጠቃቀምን የማሳደግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የቢሮውን የቴክኖሎጂ አሠራር ለማዘመን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠራ ነውም ብለዋል።

የወንጀል፣ አሥተዳደር፣ የፍትሕ እና የፍትሐብሔር ፍትሕ ሥርዓቱን በአዲስ መምራት ሌላኛው ግብ መኾኑን ነው ያነሱት። በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የአሥተዳደር ፍትሕን ማረጋገጥ ሌላኛው ሥራ መኾኑን ነው ያመላከቱት። የመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የተጠናከረ የንቃተ ሕግ ሥልጠና እና የሕግ ድጋፍ የማድረግ ሥራ መሥራታቸውንም ነው የተናገሩት። ሕገ ወጥነትን እና ሙስናን የመከላከል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የፍትሕ ተቋማትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው የተናገሩት። ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በልዩ ኹኔታ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ተሳታፊ ያልኾነበት ፍትሕ እንደማይረጋገጥም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ ለፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ እንዲኾን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለፍትሕ መረጋገጥ ምትክ የሌለው ሚና ነውም ብለዋል። የአዋጅ እና የአሠራር ሥርዓትን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ወንጀልን ለመከላከል ጥሩ ሥራ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የወንጀል ምርመራ መዛግብትን መርምሮ የመወሰን ቅልጥፋናን ማሳደጋቸውንም ተናግረዋል። ተከራክሮ የማስቀጣት ምጣኔም እያደገ ነው ብለዋል።

በሙስና ወንጀል ሊመዘበር የነበረን 337 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለሳቸውን ገልጸዋል። 47 ሺህ 862 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታም እንደተመለሰ ነው ያስገነዘቡት። በግማሽ በጀት ዓመቱ በፍትሐ ብሔር በርካታ መዛግብት ላይ ውሳኔ ማሰጠታቸውንም ገልጸዋል። ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ፍትሕ እንዲያገኙ መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ምክንያት በእስር ላይ የነበሩ ወገኖች አያያዛቸው የተስተካከለ እንዲኾን መሥራታቸውንም ገልጸዋል። በተቋሙ ውስጥ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተፈለገውን ሥራ ለመሥራት እንቅፋት እንደኾነባቸውም ገልጸዋል።

የሚዘጋጁ አዋጆች፣ መመሪያዎች ሳይጸድቁ የመቆየት ችግር እንደገጠማቸውም አንስተዋል። የፍትሕ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በተፈለገው ልክ እየሠራ አለመኾኑን የተናገሩት ኀላፊው የተሰጠው ትኩረትም አናሳ መኾኑን አንስተዋል።

ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የፍትሕ ቢሮው ችግሮች እንዲፈቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ አጀንዳ ምን አይነት ቅርጽ ሊኖረው ይችላል?
Next articleበብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተመረጡ የምክር ቤት አባላት ዝርዝር